በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቤተሰብ ሓላፊነት የወደቀባት ወጣት ተፈናቃይ


የቤተሰብ ሓላፊነት የወደቀባት ወጣት ተፈናቃይ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:28 0:00

ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለው፣ ወደ ዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የከተማዋ አስተዳደር ይገልጻል፡፡

ከተፈናቃዮቹ ውስጥ የሚበዙት ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ሲኾኑ፣ ወጣቶች ገና በለጋ ዕድሜያቸው፣ ቤተሰባቸውን የመከባከብ ሓላፊነት እንደወደቀባቸው፣ የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው ተፈናቃዮች ያስረዳሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አንዷ አምስት ቤተሰቦቿን በአንድ ጀንበር በሞት በማጣቷ ምክንያት የተፈናቅለችውንና ቀሪዎቹን ስድስት ቤተሰቦቿን የማስተዳደር ሓላፊነት የወደቀባትን፣ ወጣት ነች፡፡

የ23 ዓመቷ ወጣት ፀሐይ መኩሪያ፣ ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ተፈናቃዮች አንዷ ናት፡፡ ኪረሙ ወረዳ ተወልዳ ያደገችበት ሲኾን፣ እርሷና ከጥቃት የተረፉት ቤተሰቦቿ ከቀዬአቸው ከተፈናቀሉ አንድ ዓመት ማስቆጠራቸውን ገልጻልናለች፡፡

“እናቴን አሟት ወደ ጤና ተቋም እየወሰዷት ሳለ ከመኪና ላይ አስወርደው ቤተሰቦቼን ገድለዋቸዋል” ነበር ያለችው፡፡

ፀሐይ፥ በአድን ቀን ጥቃት አጣኋቸው ያለቻቸውን ቤተሰቦቿን በስም ትዘረዝራለች፤ “በጥቃቱ አባቴ መኩሪያው ማናዬ፣ እናቴ ትርንጎ መርእድ፣ እህቶቼ ሽብሬ መኩሪያውና ኮከብ መኩሪያው፣ የአጎቴ ልጅ ተስፋዬ በላይ በአንድ ቀን ተገድለዋል” ብላለች፡፡

ቀሪ ቤተሰቧቿን ይዛ ተወልዳ ያደገችበትን ቀዬ ጥላ ረጅም መንገድ አቋርጣ እዚኽ መድረሷን ታስረዳለች፡፡

“የሚለበስ ሳንይዝ፤ የአባይ በርሃን አቋርጠን፣ ድፍርስ ውሃ እየጠጣን፣ መንገድ ላይ እያደርን፣ ከሦስት ቀን የእግር ጉዞ በኋላ ጎጃም ደረስን፡፡ እዚያም የቀን ሥራ እየሠራሁ፣ በሰው ቤት እንጀራ እየጋገርኩ እና አረም እያረምኩ አንድ ዓመት ከቆየሁ በኋላ እዚህ ድጋፍ አለ ሲባል ከጎጃም ወደ ደብረ ብርሃን መጣሁ፡፡ እዚህ ከመጣሁ አንድ ወር ሆኖኛል፡፡”

ተወልዳ በአደገችበት ቀዬ፣ ከቤተሰቦቿ ጋራ የተሻለ ገቢ እና ኑሮ ይመሩ እንደነበር የምታስታውሰው ፀሐይ፣ ደብረ ብርሃን ከደረሰች በኋላ የኑሮው ጫና እንደከበዳት ትናገራለች።

“ደብረ ብርሃን ከመጣሁም በኋላ ቤት የለኝም፣ እጄ ላይ የነበረንን ገንዘብ ጨርሻለሁ፡፡ ስራም እንዳልሰራ የሶስት ዓመት ህጻን ልጅ አለኝ፡፡ የአራት ዓመት የእህቴን ልጅ የምንከባከበው እኔ ነኝ፡፡ ለማን ጥያቸው ሥራ ልሥራ?” ስትል ትጠይቃለች።

በመቶዎች ከሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ጋራ በአንድ መጠለያ ዳስ ውስጥ ማረፊያዋን ያደረገችውን ወጣት አካል መጎሳቆል፣ ያቀፈቻቸውን ሕፃናት መዳከም የተመለከቱ አንድ በጎ አድራጊ፣ ወደ ቤታቸው ወስደው አስጠግተዋቸው በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡

በደብረ ብርሃን ዳሸን ፋብሪካ አካባቢ ነዋሪ የኾኑት መምህር ክንፈ ይጥና፣ እነፀሐይን ጨምሮ ከ20 የማያንሱ ተፈናቃዮችን በቤታቸው አስጠልለዋቸው ይኖራሉ፡፡

“ተፈናቃዮቹን በቅርብ ስለማገኛቸው እና የደረሰባቸውን ስለማይ ውስጤ ተነካ፡፡እናም ቤቴ የተወሰኑትን በአነስተኛ ክፍያ ብዙዎቹን ደግሞ በነጻ እንዲኖሩ እያደረኩ ነው፡፡”

በመፈናቀሏ ትምህርቷን ከስድስተኛ ክፍል ያቋረጠችው የ16 ዓመቷ የፀሐይ ታናሽ እህት ሐና መኰንን፣ በሥነ ልቡና ጫን ምክንያት እህቷን መርዳት እንደተሳናት ትናገራለች፡፡

“ሰው ቤት ተቀጥሬ እየሠራሁ ነበር፡፡ ነገር ግን የራስ ህመም ሲያጋጥመኝ ሥራውን ተውኩት” ብላናለች።

የመጠለያው ጥበት ችግራቸውን እንዳባባሰባቸው ትገልጻለች፤ “በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ እስከ 14 ሰው ነው የምንኖረው፤ በአንድ ጎናችን እያደርን፡፡ ቤት ብናገኝ ያገኘነውን ጎርሰን እናድር ነበር” ብላናለች።

በሞት ያጣቻቸውን ወላጆቿንና እህቶቿን፣ “ሁሌም አስታውሳቸዋለኹ፤” ትላለች ሐና፡፡

“እህቶቼ የምንዋደድ መካሪዎቼ ነበሩ፡፡ እናትና አባቴም ተንከባክበው ነው ያሳደጉን፡፡ እነሱን በማጣቴ አይምሮዬ ይጨናነቃል፡፡ ከስምንት ቤተሰብ የተረፍነው አራት ነን፡፡”

ሐና እና ቤተሰቦቿን ጨምሮ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙት ተፈናቃዮች፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ለተፈጸመው ግድያ እና መፈናቅል፣ “ኦነግ ሸኔ” ሲሉ የጠሩትን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተጠያቂ ያደርጋሉ።

መኖሪያቸውን በቨርጂኒያ ያደረጉት የታጣቂዎቹ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል በተደጋጋሚ በሰጡት ቃል፣ ታጣቂዎቻቸው በመንግሥት ወታደሮች ላይ እንጂ በሰላማውያን ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙ ገልጸው ያስተባብላሉ። ደብረ ብርሃን ውስጥ ያገኘኋቸው፣ ፀሐይ እና እህቷ ግን ይህን የቃል አቀባዩን ማስተባበያ አይቀበሉትም።

የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ በድሉ ውብሽት ፣ ከተማዋ መቀበል ከሚገባት በላይ ተፈናቃዮችን በመያዟ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት እንዳልተቻለ ይናገራሉ።

“ከተማ አስተዳደሩ ከረጅ ተቋማት ጋር በመሆን በአቅሙ የምገባና የመጠለያ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም የተፈናቃዮች ቁጥር የመቀነስ አዝማሚያ አይስተዋልበትም፡፡ከፍተኛ የምግብና የመጠለያ እጥረት አለ፡፡” ብለዋል።

ሐናንና ስድስት ቤተሰቦቿን ጨምሮ 20 ተፈናቃዮችን በመኖርያ ቤታቸው ያስጠጉት መምህር ክንፈ በበኩላቸው፣ ሰው ሁሉ በቻለው ዐቅም በመሥራት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፤ በማለት ያሳስባሉ። “መንግሥት ባለሃብቱና በጎ አድራጊዎች በተለይ ለተራቡት ሊደርሱ ይገባል” ሲሉም አክለዋል።

ለቤተሰቧ ሦስተኛ ልጅ የኾነችው ፀሐይ፣ ታላላቆቿ በመገደላቸው ቤተሰቧን የማስተዳደር ሓላፊነት እንደወደቀባት ትናገራለች፡፡

“የሰባትና የአራት ዓመት የእህቶቼ ልጆች፣ የራሴን የሦስት ዓመት ህጻን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ እያስተዳደርኩ ነው፡፡ ከባለቤቴ ጋር ደግሞ ተለያይተናል፡፡” ያለችው ፀሐይ “አገሬ እናትና አባቴ ከጎኔ ነበሩ፡፡ ቤታችንም ሙሉ ነበር፡፡ እዚህ ግን ሁሉም ነገር የለም፡፡ ከህጻናቱ ተደብቄ ሌሊቱን ሳለቅስ ነው የማድረው፡፡ አሁን ሁሉም ጫና የወደቀው እኔ ላይ ነው።

የሚደግፈኝ በምክር የሚያግዘን ታላቅ እህትና ወንድም የለኝም፡፡ የምኖረው ለህጻናቱ ስል እንጂ ያለንበት ሁኔታ መኖር አያስመኝም፡፡” ብላናለች።

“መፈናቀሉ ከአደረሰብኝ ጉዳት ሳላገግም፣ እኔ ጋራ ያለው የእህቴ ልጅ ለሕመም በመዳረጉ፣ ሌላ ፈተና ኾኖብኛል፤” ያለችው ፀሐይ፣ የድጋፍ ጥሪ ድምፅዋን አሰምታለች፡፡

“እኔ ጋር ያለው የሰባት ዓመት የእህቴ ልጅ ዓይኑን ያመዋል፡፡ አንድ ዓይኑም አያይለትም፡፡ እሱን የሚያሳክምልኝ ደጋፊ ባገኝ መልካም ነበር፡፡” ስትል ፍላጎቷንም አጋርታለች።

ፀሐይ እና ቤተሰቧ መንግሥት ሰላም አስፍኖ ተወልደው ወደ አደጉበት ቀያቸው እንዲመልሳቸው ይፈልጋሉ።

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያዎች የሰፈሩ 30 ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንዳሉ፣ የከተማ አስተዳደሩ ያመለክታሉ፡፡

ዓለም አቀፉ የተፈናቃዮች ቁጥጥር ማዕከል(IDMC)፣ ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው ሪፖርቱ፣ በርካታ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ካሉባቸው ሀገራት፣ ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚዋ አገር አድርጎ አስቀምጧት ነበር፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት(OCHA) ጨምሮ፣ ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች የሚያወጧቸው ሪፖርቶች እንደሚያስረዱት፣ በኢትዮጵያ የሰዎች መፈናቀል ቀጥሏል፡፡ በዚኽ ደግሞ ቀዳሚ ተጎጅዎቹ ሕፃናት፣ ሴቶች እና የዕድሜ ባለጸጎች እንደኾኑ ተገልጿል፡፡

XS
SM
MD
LG