ዋሽንግተን ዲሲ —
በሱዳን የአልጀዚራ የዜና ማሰራጫ ቢሮ ዋና ኃላፊ በሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ትናንት እሁድ መታሰራቸውን መሠረቱን ኳታር ያደረገው አልጀዚራ አስታውቋል፡፡
አልጀዚራ ባስተላለፈው የትዊት መልዕክት፣ በመላው ሱዳን ባላፈው ቅዳሜ የተደረገውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ በማግስቱ የቢሮው ኃላፊ ሙሳልሚ ኢል ካባሺ መኖሪያ ቤት፣ በጸጥታ ኃይሎች መወረሩንና በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጿል፡፡
በሱዳን የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን የሱዳን ጸጥታ ኃይሎች ተኩስና አስለቃሽ ጋዝ መጠቀማቸው የተገለጸ ሲሆን የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ ለተቃውሞ ከወጡት መካከል የ15 ዓመት ልጅ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ ማለፉን አስታውቋል፡፡
አልጀዚራ ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ ያወጣ ሲሆን ለጋዜጠኛው ደህንነት የሱዳን ወታደራዊ ክፍል ተጠያቂ ነው ብሏል፡፡
አስተያየት እንዲሰጡበት የሱዳን ባለሥልናትን ማግኘት አልተቻለም፡፡