በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ የመንግሥት ሠራተኞች ከደቡብ ሱዳን እንዲወጡ አዘዘች


ፋይል - የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር በቀኝ እና ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር በግራ ከሁለት ዓመት በፊት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ በጁባ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በጁባ አደባባይ ላይ በተሰናዳ ዝግጅት ላይ።
ፋይል - የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር በቀኝ እና ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር በግራ ከሁለት ዓመት በፊት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ በጁባ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በጁባ አደባባይ ላይ በተሰናዳ ዝግጅት ላይ።

ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ሱዳን ውስጥ እየታየ ያለው ውጥረት እየበረታ በመምጣቱ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ውጪ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ፣ ዛሬ በአወጣው የአስቸኳይ ጊዜ የጉዞ ማስጠንቀቂያ፣ በደቡብ ሱዳን ጦርነቱ መቀጠሉንና፣ ሕዝብ በቀላሉ ሊያገኛቸው የሚችላቸው የጦር መሳሪያዎች መኖራቸውን በማመላከት፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ያልኾኑ የመንግሥት ሠራተኞች በሙሉ ከደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ እንዲወጡ አዟል።

ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር ጋራ ጥብቅ ግንኙነት ያለው የታጠቀ ቡድን ማክሰኞ ዕለት በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ ወረራ ማካሄዱን ተከትሎ፣ ለማቻር ታማኝ የነበሩት የጦሩ ምክትል አዛዥ ጀነራል ጋብሪኤል ዱፕ ላም እና ሁለት ሚኒስትሮች ለእስር ተዳርገዋል።

ማቻር፤ ባለፈው ወር በርካታ አጋሮቻቸው ከመንግስት ሹመት መባረራቸው እ.አ.አ በ2018 በእሳቸው እና በፖለቲካ ተቀናቃኛቸው ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ ይጥላል ብለው ነበር። በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል ለአምስት ዓመት ዘልቆ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ከ400 ሺሕ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ለማቻር ታማኝ የነበሩት የጦሩ ምክትል አዛዥ ጀነራል ጋብሪኤል ዱፕ ላም በሰሜን በተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ማክሰኞ እለት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በተመሳሳይ የማቻር አጋር እና የፔትሮሊየም ሚኒስትር የሆኑት ፑት ካንግ ቾል ከጠባቂዎቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ረቡዕ ዕለት በቁጥጥር ስር ውለዋል። ለእስር የተዳረጉበት ምክንያት ግን እስካሁን አልተገለጸም።

የምዕራብ ሀገራት ልዑካን መሪዎቹ ውጥረቱን እንዲያረግቡ ባለፈው ሳምንት አሳስበው ነበር።

ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ በ2018 የተደረሰውን ስምምነት እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ያላደረገች ሲሆን ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው ምርጫም በገንዘብ እጦት ምክንያት ለሁለት ዓመት ተራዝሟል።

አርብ ዕለት ሲቪሎችን በማስወጣት ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ የነበረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሄሊኮፕተር፣ ላይ የተፈፀመ ጥቃት የጸጥታ ሁኔታውን የበለጠ ያወሳሰበው ሲኾን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች የደቡብ ሱዳን ቢሮ ፣ ድርጊቱ እንደ ጦር ወንጀል የሚቆጠር መኾኑን ተናግረዋል። በደቡብ ሱዳን ሰሜኑ ክፍል እና በመዲናይቱ ጁባ ያለው ውጥረት በሀገሪቱ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ሊያደናቅፈው ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።

ደቡብ ሱዳን ውስጥ ለዓመታት የዘለቀውን የሰላም ስምምነት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ኹኔታቸው እየተከሰቱ መኾኑን የሚያሳዩ ምልክቶችን እያዩ መኾኑን ፣ የገለጹት ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ያስሚን ሱካ፣ "መሪዎቹ መለያየትን እና ግጭትን ከማባባስ ይልቅ በሰላም ሂደቱ ላይ በአስቸኳይ አተኩረው፣ የደቡብ ሱዳን ዜጎችን ሰብአዊ መብት ማስከበር እና ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት መሸጋገርን ማረጋገጥ አለባቸው" ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG