ሳግ እየተናነቃቸው የተናገሩት የዩናይትድ ስቴትስ የአገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊ፣ ቁጥራቸው 6 ሺሕ የሚጠጋ ሠራተኞች ከሥራ እንደሚባረሩ ይፋ እንዳሳወቋቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ለሮይተርስ የዜና ወኪል በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል። ይህም ሥራ በሚበዛበት የግብር መክፈያ ሰሞን የተወሰደ እርምጃ ከ6 በመቶ በላይ የሚሆነውን የድርጅቱን የሰው ኃይል የሚያሳጣ መሆኑ ተመልክቷል።
የሰው ኃይል ቅነሳው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ የመንግሥት ሠራተኞችን ቁጥር ለመቀነስ የያዙት ጥረት አካል ሲሆን፣ የባንኮችን ሥራ የሚቆጣጠሩ፣ የደን ጥበቃ እና እንክብካቤ ሠራተኞች፣ የሮኬት ሳይንስ አዋቂ ሳይንቲስቶች እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ላይ የተነጣጠረ መሆኑ ታውቋል። ይህን የማስፈጸሙም ሥራ የሚመራው በፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ዋነኛ ለጋሽ በነበሩት ቢሊነሩ ኢላን መስክ ነው።
መስክ ሜሪላንድ ክፍለ ግዛት ‘ኦክሰን ሂል’ ውስጥ በሚገኘው ናሽናል ሃርበር የተባለ ሥፍራ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የሪፐብሊካን የፖለቲካ ፓርቲ አቀንቃኞች እና ባለሥልጣናት የሚሳተፉበት ዓመታዊ ጉባኤ መድረክ የመንግሥታቸውን ወጪ ለመቀነስ ባራመዷቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ፖሊሲዎቻቸውን ከሚታወቁት የአርጀንቲና ፕሬዝደንት ጃቪየር ሚሌ እርምጃቸውን ጥንካሬ ለማሳየት የብረት መጋዝ በስጦታ ሲቀበሉ ታይተዋል።
"ይህ ቢሮክራሲ የሚቆረጥበት መጋዝ ነው" አሉ መስክ የመንግሥት ሠራተኞችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን የቀነሱበትን እርምጃ ለማመላከት በሚመስል አኳሃን፣ መድረኩ ላይ እንደቆሙ ብርቱውን መቁረጫ ወደ ላይ ከፍ አድርገው እያሳዩ። የሠራተኛ ማኅበራት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል ሠራተኞች ሥራቸውን እንደሚያጡ እየተነገራቸው ያለበትን በጅምላ ከሥራ የማስወጣት ርምጃ ለማስቆም በፍርድ ቤት ክስ አቅርበዋል። ይሁንና አንድ ጉዳዩን ያዩ የዋሽንግተን የፌዴራል ዳኛ በትላንትናው ዕለት በሰጡት ብይን ለአሁኑ መቀጠል እንደሚችሉ የሚፈቅድ ብይን አሳልፈዋል።
የአገር ውስጥ ገቢ የባለሞያዎች ቅጥር ድሬክተር ክሪስቲ አርምስትሮንግ 6ሺሕየሚጠጉ ባልደረቦቻቸው ከድርጅቱ የሰው ኃይል እንደሚቀነሱ በስልክ ባሳወቁበት ወቅት፤ ‘እምባ እየተናነቃቸው’ እንደነበር መልዕክቱ በተላለፈበት ወቅት የነበሩ አንድ ሠራተኛ ገልጸዋል። እርስ በርስ እንዲደጋገፉ ያበረታቱት ኃላፊ "በእጅጉ በስሜት ተነክተው እንደነበር" መልዕክቱን የተከታተሉት ሠራተኛ አክለው አመልክተዋል።
አንድ የጉዳዩ አዋቂ እንደገለጹት፤ የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤቱ ቅነሳው በአጠቃላይ 6,700 ሠራተኞችን እንደሚመለከት እና በዋናነትም የባለ ጸጋ ግብር ከፋዮችን የግብር ኃላፊነት ለማስፈጸም በተያዘ ጥረት ለማጎልበት በሞከሩት በዲሞክራቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሥራ ማስፋፊያ ዕቅድ በተቀጠሩ የድርጅት ሰራተኞች ላይ የተነጣጠረ መሆኑ ተጠቁሟል። ከሪፐብሊካን ወገን የሆኑ በተራ አሜሪካውያን ላይ አላስፈላጊ ጫና ይፈጥራል በሚል ርምጃውን ተቃውመዋል።
የግብር ሰብሳቢው ድርጅት በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው 100 ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞች ሲኖሩት፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2021 ባይደን ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት የነበት ሠራተኞች ቁጥር 80 ሺሕ ነበር።
ከየትኛውም ፓርቲ ወገን ያልሆኑ የበጀት ጉዳይ አዋቂዎች ባይደን እንዲያድግ ያደረጉት የሠራተኛ ኃይል የመንግስቱን ገቢ በማሳደግ፣ በትሪሊዮን ዶላር የሚሰላውን የበጀት ክፍተት ለማጥበብ ያግዛል የሚል ግምት ሰጥተው ነበር።
የሠራተኛ ኃይሉን ለመቀነስ የተወሰደውን ርምጃ “ይህ እንደ እውነቱ የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤቱ በባለ ጸጋ ግብር ከፋዮችን ሳይሆን፤ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ትኩረት ማድረግ የመረጠ ድርጅት እዲሆን ያደርገዋል” ብለዋል፡፡
የፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ የግብር ጉዳዮችን የሚመለከተው ሕግ መምህሩ ፕሮፌሰር ፊሊፕ ሃክኒ። "እጅግ አሳዛኝ ድርጊት ነው" ሲሉ አክለዋል፤ ካሁን ቀደም የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤቱ ነገረ ፈጅ በመሆን ያገለገሉት ፕሮፌሰር ሃክኒ።
ከሥራ ከተባረሩት ውስጥ የግብር ክፍያ ሰብሳቢዎች፣ የደንበኛ አገልግሎት ፣ሠራተኞች፣ የግብር ክፍያ ይግባኝ የሚሰሙ ባለሞያዎች እና እንዲሁም የመረጃ ቴክኖሎጂ ሰራተኞች ይገኙባቸዋል። ርምጃው በ50ውም የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ውስጥ ባሉ ሠራተኞች ላይ ተጽእኖ ያሳድራል ሲሉ ሮይተርስ ያነጋገራቸው ምንጮች አመልክተዋል። የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት በበኩሉ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ዓመታዊው የግብር ሂሳብ የሚወራረድበት ወቅት ገና በመጋመስ ላይ በመሆኑ፤ አይርኤስ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት የተሻለ ጥንቃቄ የታየበት አካሄድ ተከትሏል፤ ያሉት ምንጮች፣ በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ስሌት መሰረት እስከ ሚያዝያ 15 አጋማሽ በሚዘልቀው የሥራው ማጠናቀቂያ ድረስ ከ140 ሚሊዮን በላይ በግል ግብር የሚከፍሉ ሰዎችን የግብ ክፍያ ተመላሽ ማስፈጸም ስለሚጠበቅበት፣ ለዚያ ሥራ ወሳኝ ናቸው የተባሉትን በርካታ ሺሕ ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው እንደሚያቆይ አንድ ምንጭ ጠቁመዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የፌዴራል ሠራተኞችን ከሥራ የማሰናበቱ ርምጃ ለሥራ ኃላፊነቱ አዲስ በሆኑ እና ረጅም ጊዜ ካገለገሉ ሠራተኞች አንጻር ሲታይ አነስተኛ ጥበቃ ያላቸው ሰራተኞች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ ዋይት ሀውስ የዩናይትድ ስቴትስ የፖስታ አገልግሎት መስሪያ ቤትን የሥራ አመራር ለመበተን እና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድረውን ድርጅት በንግድ ጉዳዮች ሚንስቴር ሥር እንዲተዳደር ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ትላንት ሃሙስ ዘግቧል።
በሌላ በኩል “በካንሳስ ከተማ የሚገኘው የአይአርኤስ ጽሕፈት ቤት የሙከራ ጊዜያቸውን ያላጠናቀቁ ሠራተኞች ስንብታቸውን የሚያረግጋጠውን ደብዳቤ ከሚቀበሉበት የኢሜል መልዕክት መላላኪያ በስተቀር፤ ማናቸውንም ሌሎች ተግባራት የሚያከናውኑባቸው የኮምፒውተሮቻቸው ቁልፎች በሙሉ ተዘግተው ነው የጠበቋቸው” ሲሉ የፌድራሉ የሠራተኛ ማኅበር የአካባቢው ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ሻነን ኢሊስ ተናግረዋል።
ኤሊስ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል "የአሜሪካ ሕዝብ በእውነት ሊገነዘበው የሚገባው ነገር በአገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት የሚሰበሰበው ገንዘብ በኅብረተሰባችን ውስጥ በየቀኑ የምንገለገልባቸውን የተለያዩ ፕሮግራሞችን የሚደግፉ ናቸው” ብለዋል።
ዋይት ሀውስ ቁጥሩ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከሚደርሰው የመንግሥት ሠራተኛ ምን ያህሉን በከፍተኛ ቁጥር በጅምላ ከሚፈጸመው ከሥራ የማሰናበት ርምጃው እንደሚያካትት አላስታወቀም። ቁጥራቸው 75 ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞች ራሳቸውን በፈቃዳቸው ከሥራ እንዲያሰናብቱ የቀረበውን ዕቅድ መፈረማቸው ባለፈው ሳምንት ተዘግቧል።
አስተዳደሩ የያዘው የወጪ ቅነሳ ዕቅድ ‘መንግሥት የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች ሊጎዳ ይችላል’ በሚል አያሌ አሜሪካውያን የሚጨነቁ መሆናቸውን ሮይተርስ እና ኢፕሶስ በጋራ ያሰባሰቡት እና ትላንት ሐሙስ ይፋ የተደረገ የሕዝብ አስተያየት መረጃ ጠቁሟል።
መድረክ / ፎረም