አሜሪካዊው የቴክኖሎጂ ቱጃር ኤሎን መስክ ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመኒ (ኤ.ኤፍ.ዲ) ወይም በግርድፉ አማራጭ ለጀርመን የተሰኘውን ጸረ-ስደተኛ ፓርቲ፤ በድጋሚ መደገፉን ተከትሎ፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን ትላንት ቅዳሜ የተቃውሞ ሰልፍ ወጥተዋል። በጀርመን በሚቀጥለው ወር የሕግ አውጪዎች ምርጫ ይካሄዳል።
መስክ፣ በምሥራቅ ጀርመን ሃሌ ከተማ በሺዎች ለሚቆጠሩ የኤ.ኤፍ.ዲ ደጋፊዎች በቪዲዮ ባደርገው ንግግሩ፤ ፓርቲያቸው “ለወደፊቷ ጀርመን ሰናይ ተስፋ” ነው ሲል ተናግሯል።
ኤሎን መስክ የቪዲዮ ንግግሩን ሲያደርግ የፓርቲው አጋር መሪ አሊስ ቫይደል ፈገግ እያሉ ሲመለከቱ የታዩ ሲሆን፤ የሰልፉ ተሳታፊ የነበሩት የኤ.ኤፍ.ዲ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ድጋፋቸውን በጩኸት አሳይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በበርሊን እና በኮሎኝ ከ35 እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ሰልፈኞች እንደሚሆኑ ፖሊስ የገመታቸው ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ተቃዋሚዎች ትዕይንተ ሰልፍ አድርገዋል።
በበርሊን ለተቃውሞ የወጡት ሰልፈኞች “ለዴሞክራሲ የበራ የብርሃን ባህር” ሲሉ የሞባይል የስልኮቻቸውን መብራቶች በማብራት በጀርመን ታሪካዊ ስፍራ በሆነው ብራንደር በርግ ግንብ ጋር “መከላከል” የሚል ጽሁፍ ይዘው ወጥተዋል።
ኤ.ኤፍ.ዲ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ለብዙ አስርት ዓመታት ነውር ሆኖ የዘለቀውን ቀኝ ዘመም ፓርቲ ድጋፍ ማሳያት በተለየ መልኩ፤ በዚህ ዓመት 20 ከመቶ የሚሆን የህዝብ ድጋፍ በመያዝ ከመጭው ምርጫ በፊት ሪከርድ ሰብሯል።
በተመሳሳይ የኤሎን መስክ የቅርብ አጋር የሆኑት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኤ.ኤፍ.ዲድ ፓርቲ ደጋፊዎች ምርጫው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው “እንደሚመስለኝ ምርጫው የአውሮፓን አጠቃላይ ዕድል፣ ምናልባትም የአለምን እጣ ፈንታ ይወስናል” ብለዋል።
መስክ በብሪታኒያ የሚገኙትን ጨምሮ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የአውሮፓ ፖለቲከኞችን በማህበራዊ መድረኩ ኤክስ በመጠቀም አስተያየት በመስጠት ሲያጨናንቅ ተስተውሏል። ኤ.ኤፍ.ዲ ፓርቲ ልክ እንደ ትራምፕ ሁሉ የስደተኞች ፍልሰት የሚቃወም፣ የአየር ንብረት ለውጥ የለም የሚል፣ የጾታ ፖለቲካን የሚቃወም፣ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የሀሳብ ነጻነትን የሚጥሱ ናቸው በማለት የሚኮንን ፓርቲ ነው።
መድረክ / ፎረም