በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአርበኞች መካነ መቃብር እንዲሆን የታጸነው ጥንታዊው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል


የአርበኞች መካነ መቃብር እንዲሆን የታጸነው ጥንታዊው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:39 0:00

የአርበኞች መካነ መቃብር እንዲኾን የታጸነው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እድሳት ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ተጠናቆ ሕንጻው ተመርቋል። ከ1924 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታው መጀመሩን በካቴድራሉ ድረ ገጽ ላይ የሰፈረው ጹሑፍ ያስረዳል። “አስደናቂ የኪነ - ሕንጻ ንድፍ” እንዳለው የሚነገረው ሕንጻ የመጀመሪያው መሰረተ ድንጋይ የተጣለውም በቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሠ ቀዳማዊ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ የንግስና ዘመን ነው።

ግንባታው ሳይጠናቀቅ ኢትዮጵያ በጣሊያን በመወረሯ፣ ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ዓመታት ግንባታው ተቋርጦ መቆየቱን ጹሑፍ ያስረዳል፡፡

ጣሊያን በጦርነቱ ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ከወጣ እና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ ከሁለት ዓመት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ ከ81 ዓመት በፊት ጥር 7 ቀን 1936 ዓ.ም መመረቁን ለታሪክ በተቀመጠው ሰነድ ላይ ሰፍሯል።

ካቴድራሉ ከተመረቀ ከ81 ዓመታት በኋላ ከሁለት ዓመት በላይ የፈጀ ዕድሳት ተደርጎለታል። አብዛኛው የእድሳቱ ሥራም ተጠናቆ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና በብፁአን አባቶች ተመርቆ ታቦተ ሕጉ ወደ መቅደሱ ተመልሶ ገብቷል።

እድሳቱ 200 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገዘብ ቫርኔሮ ኮንስትራክሽን በተባለ ተቋራጭ መከናወኑን የካቴድራሉ ዋና ጸሐፊ ላዕከ-ሰላም ሽታው ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡
የካቴድራሉ ዋና ጸሐፊ፣ ላዕከ-ሰላም ሽታው ብርሃኑ፣ በወቅቱ በነበሩት የኢትዮጵያ መሪ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ በአስተላለፉት ውሳኔ፣ ለሀገራቸው ነጻነት ሲታገሉ ሕይወታቸውን ያጡ አርበኞች አርበኞች መካነ ዕረፍታቸው በዚሁ ካቴድራል እንዲኾን መደረጉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያን እስከ ሀገር መሪነት ያገለገሉትን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ ፣ቤተ ክህነትንም በከፍተኛ ኃላፊነት የመሩ የሃይማኖት አባቶች መካነ መቃብራቸው የሚገኘው በካቴድራሉ ውስጥ መኾኑን አክለው ገልጸዋል።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን እና ባለቤታቸውን እንዲሁም የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በተለያየ ኃላፊነት ያገለገሉ መሪዎች እና የነጻነት ታጋዮች፣ የተለያዩ የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርኮች መካነ ዕረፍታቸው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መሆኑን የካቴድራሉ ኃላፊዎች ለአሜሪካ ድምጽ ገልጸዋል።

ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ጉልህ ታሪካዊ ትርጉም ያለው እና ከኪነ-ሕንጻው ጀምሮ በውስጡ በርካታ ቅርሶችን የያዘው ካቴድራሉ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው መኾኑንም አስረድተዋል፡፡

ቤተ ክርስትያኗ የራሷን ፓትርያርክ መሾም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የቅዱሳን ፓትርያርኮችና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሹመት እና በዓለ ሲመት የሚፈጸመው በካቴድራሉ ነው፡፡
በዚህ ካቴድራል ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች የተሳሉት ብሥዕሎች፣ ስለነፃነት የተደረጉ ታሪካዊ ሂደቶችን በማመላከት የታሪክ አሻራነታቸውን ለትውልድ በማስተላለፍ ላይ አንደሚገኙም ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG