ቻይና የዩናይትድ ስቴትስ ወደ ውጭ የሚላከውን የሰው ሰራሽ ልህቀት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በሚመለከት ያወጣቻቸውን አዳዲስ የቁጥጥር እርምጃዎች “በጽኑ እንደምትቃወም” ገልጻ የኩባንያዎቿን ጥቅም ለመጠበቅ “ቆራጥ እርምጃዎችን” እንደምትወስድ አስታውቃለች።
የባይደን አስተዳደር ትላንት ሰኞ የሰው ሰራሽ ልህቀትን ለማዳበር የሚያገለግሉ ቺፕስ የተባሉትን ልዩ የዘመናዊ ኮምፒውተር ክፍሎችን ወደ ውጭ መላክን አስመልክቶ አዲስ የቁጥጥር ማዕቀፍ አቅርቧል።
ርምጃው ከአምራቾች እና ከሌሎች ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር ተያይዘው በቴክኖሎጂው ላይ የሚከሰቱ የብሔራዊ የደህንነት ስጋቶችን ሚዛን ለመጠበቅ የሚደረግ ሙከራ መሆኑም በአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ ተጠቅሷል፡፡
አዲሱ ደንብ አብዛኛው ትኩረቱ ቻይና ላይ ቢሆንም ሜክሲኮ፣ ፖርቱጋል፣ እስራኤል እና ስዊዘርላንድ ለሰው ሠራሽ ልህቀት መረጃ ማዕከላት እና ምርቶች የሚያስፈልጉ ቺፖች ተደራሽነት ገደብ ከሚገጥማቸው ሀገራት መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን አሜሪካ ቻይናን በ“እኩይ ዓላማ” ትከተላታለች ሲሉ ከሰዋታል፡፡ ቃል አቀባዩ አያይዘው “የዓለም አቀፉን የኢንዱስትሪ እና የአቅርቦት ሰንሰለቶች መረጋጋት የሚያናጋ፣ የሁለቱን ሀገራት ጥቅም እና የሁሉም አገሮች የንግድ ዘርፎች የሚጎዳ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ውሳኔው የተደረገው ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ሥራ ከመጀመራቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ መሆኑ ነው፡፡
የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሰለቫን “በጭራሽ በፓርቲ ወገንተኝነት የሚታይ ጉዳይ መሆን የለበትም” ብለው ያለውን አካሄድ መከተል ወይም መተው የትረምፕ ፋንታ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እገዳ የተደነቀነበት ቲክ ቶክ፣ ብዙዎቹ ተጠቃሚዎች፣ ሲያሆምሹ ወደተባለው ወደ ሌላኛው የቻይና መተግበሪያ እየፈለሱ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ መተግበሪያው በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ የአፕል ስልክ ተጠቃሚዎች ወደ ስልኮቻቸው ከጫኑት መተግበሪያ ትልቁ መሆኑን የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ሲያምሹ ቀጣዩ የአሜሪካ ኢላማ ሊሆን ይችል እንደሆነ የተጠየቁት ቃል አቀባዩ “መላ ምት አዘል ለሆኑ ጥያቄዎች” ብለው በመደቧቸው ውስጥ የሚካተት በመሆኑ ምላሽ እንደማይሰጡበት በመግለጽ አልፈውታል፡፡
መድረክ / ፎረም