በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዱባይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይ ኾነዋል


በውድድሩ በሴቶች ከአንድ እስከ ሦስት የወጡት በዳቱ ሂርጳ ደራ ዲዳ እና ትዕግስት ግርማ
በውድድሩ በሴቶች ከአንድ እስከ ሦስት የወጡት በዳቱ ሂርጳ ደራ ዲዳ እና ትዕግስት ግርማ

ዛሬ እሑድ ጥር 4 ቀን በተካሔደው የ2025 የዱባይ ማራቶን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን ከአንደኛ እስከ አሥረኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡

በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ባለው የዱባይ ማራቶን፣ በወንዶች ምድብ አሸናፊ የኾነው በማራቶን የመጀመሪያ ውድድሩን ያደረገው ቡቴ ገመቹ ሲኾን በሴቶቹ በዳቱ ሂርጳ አሸንፋለች፡፡

ባለፈው ሰኔ ወር በቻይና ጉይዡ ዜኒንግ የግማሽ ማራቶን ውድድርን ያሸነፈው የ23 ዓመቱ አትሌት ቡቴ፣ የ ዛሬውን የዱባይ ማራቶችን ለማጠናቀቅ 2፡04፡51 የሆነ ጊዜ ወስዶበታል፡፡

በዱባይ የተገኙ የኢትዮጵያውያኑ ደጋፊዎች የሀገራቸውን ባንዲራ በማውለብለብ ደስታቸውን ሲገልጹ
በዱባይ የተገኙ የኢትዮጵያውያኑ ደጋፊዎች የሀገራቸውን ባንዲራ በማውለብለብ ደስታቸውን ሲገልጹ

በወንዶቹ የመጀመርያዎቹን 14 ደረጃዎች ኢትዮጵያውያን በያዙበት በዚህ ውድድር ከቡቴ በ23 ሰከንድ ዘግይቶ የገባው ብርሃኑ ፀጉ ነው፡፡ አትሌት ሺፈራ ታምሩ ደግሞ ውድድሩን በሦስተኝነት አጠናቋል፡፡ኬንያዊው የቀድሞ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ዴኒስ ኪሜቶ 15ኛ በመውጣት ከ1-15 ባለው ደረጃ ውስጥ የገባ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ብቸኛው አትሌት ነው፡፡

በዳቱ ሂርፓ አንደኛ በወጣችበት በሴቶች ውድድር፣ የ2023 አሸናፊዋ የታምራት ቶላ ባለቤት ዴራ ዲዳ ሁለተኛ ወጥታለች፡፡ የ25 ዓመቷ አትሌት በዳቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን በከፍተኛ መጠን አሻሽለ ውድድሩን 2፡18፡27 በሆነ ሰአት ማጠናቀቋን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያሳያል፡፡

በሴቶቹ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹን 16 ደረጃዎች ይዘው ባጠናቀቁበት በዱባይ ማራቶን ሦስተኛ የወጣችው ትግስት ግርማ ናት፡፡

በሁለቱም ምድቦች አንደኛ የወጡ አትሌቶች እያንዳንዳቸው 80 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ሲሸለሙ ሁለተኛ እና ሦስተኛ የወጡት ደግሞ እያንዳንዳቸው 40 ሺህ እና 20ሺህ ዶላር መሸለማቸውን የውድድሩ አዘጋጆች መረጃ ያሳያል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG