በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኒው ኦርሊንስ በመኪና የተፈጸመው ጥቃት እንደ ሽብር ጥቃት በመመርመር ላይ ነው


በኒው ኦርሊንስ በመኪና የተፈጸመው ጥቃት እንደ ሽብር ጥቃት በመመርመር ላይ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:02 0:00

በኒው ኦርሊንስ በመኪና የተፈጸመው ጥቃት እንደ ሽብር ጥቃት በመመርመር ላይ ነው

የሟቾች ቁጥር 15 ደርሷል

በአሜሪካ ሉኢዚያና ግዛት፣ ኒው ኦርሊንስ ከተማ ውስጥ ዐዲሱን ዓመት ለማክበር ተሰባስበው በነበሩ ሰዎች ላይ አንድ አሽከርካሪ መኪናውን በፍጥነት በመንዳት 15 ሰዎችን የገደለበትና ቢያንስ 35 ሰዎችን የጎዳበት ድርጊት እንደ ሽብር ተግባር ተቆጥሮ በመመርመር ላይ መኾኑን የፌዴራል ምርመራ ቢሮው (ኤፍ ቢ አይ) አስታውቋል።

አሽከርካሪው ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ መኪናውን አቁሞ ከፖሊሶች ጋራ ባደረገው የተኩስ ልውውጥ ሊገደል ችሏል። በቴክሳስ ግዛት የተወለደው የ42 ዓመቱ ሻምሱድ-ዲን ጃባር የሠራዊት ዓባል የነበረና ከ10 ዓመታት በፊት የተሰናበት መሆኑ ታውቋል።

ተከራይቶት በነበረው ክፍት ወይም ፒክ አፕ መኪና የኋላ መጎተቻ ላይ የእስላማዊ መንግሥት ወይም አይሲስ ባንዲራን እያውለበለበ ‘በርበን ስትሪት’ ተብሎ በሚጠራውና በበዓላት ብቻ ሳይሆን፣ በአዘቦቱም ቀን ሞቅ ደመቅ በሚለው መንገድ ላይ ዐዲሱን ዓመት ለመቀበል ተሰባስበው በነበሩ ሰዎች ላይ መኪናውን በፍጥነት አሽከርክሮ ቢያንስ 15 ሰዎችን ገድሎ 35 የሚሆኑት ላይ ጉዳት አድርሷል።

የሻምሱድ-ዲን ጃባር ጥቃት በላስ ቬጋስ ከተማ በሚገኘው የትረምፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ደጃፍ ላይ በእሳት ከወደመው የሳይበርትራክ መኪና ጋራ ግንኙነት ይኖረው እንደሁ ባለሥልጣናት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስታውቀዋል። መኪናው ርችቶችና ነዳጅ እንዲሁም ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮችን ጭኖ የነበረ ሲሆን በፍንዳታው አንድ ሠው ሲሞት ሰባት የሚሆኑት ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሻምሱድ-ዲን የአይሲስ ቡድን ዓላማዎች እንዳነሳሱት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስታውቋል። ፕሬዝደንት ባይደን በዚሁ ጉዳይ ላይ ትላንት በሰጡት አስተያየት፣ “ጥቃቱን ከመፈጸሙ ጥቂት ሰዓታት በፊት በአይሲስይ እንደተበረታታና ሰዎችን መግደል እንደሚሻ በማኅበራዊ ሚዲያ በለቀቀው ቪዲዮ ማስታወቁን የፌዴራል ምርመራ ቢሮው (ኤፍ ቢ አይ) አሳውቆኛል። የአይሲስ ባንዲራ ጥቃቱን ለመፈጸም በተከራየው መኪና ላይ ተገኝቷል።” ብለዋል።

የፌዴራል ምርመራ ቢሮው (ኤፍ ቢ አይ) ድርጊቱን እንደ ሽብር ጥቃት ቆጥሮ በምርመራ ላይ መሆኑን ያስታወቀው ወዲያው ነበር። የኤፍቢአይ ልዩ ረዳት መርማሪ አሌቲያ ደንካን

“እንደ ሽብር ጥቃት ወስደን ለመመርመር ከአጋሮቻችን ጋራ በመሥራት ላይ ነን። ከግለሰቡ ጋር ተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ የምንላቸውን ሰዎች ለማግኘት በመሥራት ላይ ነን። ሌላ ስጋት እንዳይኖር ለማረጋገጥ እየሠራን ነው። ሻምሱድ-ዲን ጃባር ብቻውን ኃላፊነት ይወስዳል ብለን አናምንም። የሚታወቁ የግለሰቡ የቅርብ አጋሮችን ጭምሮ ሌሎችንም ፍንጮችን በሙሉ እየመረመርን ነው።” ብለዋል።

ከጥቃቱ ጋራ በተገናኘ በተደረገው ምርመራ፣ ሦስት ወንዶች እና አንዲት ሴት ፈንጂ ሲያስቀምጡ የሚያሳየውን ቪዲዮ ያገኙ መርማሪዎች ተጨማሪ ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ይህም ባለሥልጣናት ሻምሱድ-ዲን ጃባር ብቻውን አልነበረም ለሚለው ጥርጣሬያቸው ምክንያት እንደሆነ ተገምቷል።

ሻምሱድ-ዲን ጃባር ለመኖሪያ ቤት ከባንክ ለተበደረው የሚከፍለው ወርሃዊ ክፍያ በ27 ሺሕ ዶላር ወደ ኋላ የቀረ መሆኑና ፍቺውን በአስቸኳይ መፈጸም ይፈልግ እንደነበር የፍቺ ሰነዶች አመልክተዋል።

“ብድሩን በየወሩ ለመክፈል ሁሉንም መንገድ ሞክሬያለሁ፣ ያለን አማራጭ ቤቱን መሸጥ ወይም በዕዳ እንዲያዝ ማድረግ ነው፣” ሲል በአንድ ወቅት ለቀድሞ ባለቤቱ ጠበቃ በጻፈው ኢሜይል ላይ ገልጿል።

ፍቺው ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ተጠናቋል። የቤት አሻሻጭነት ሥራውም የተሳካ አልነበረም። አንደኛው ኩባንያ ባለፈው ዓመት 28ሺሕ ዶላር ሲከስር፣ ሌሎች የጀመራቸው ሁለት ኩባንያዎች ምንም ያልተንቀሳቀሱ መሆኑ ታውቋል።

ጥቃቱ በአይሲስ አነሳሽነት የተፈጸመ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ በአሜሪካ ምድር ላይ ከዓመታት ወዲህ የተፈጸመና በርካታ ሞትን ያስከተለ ጥቃት ተደርጎ ይመዘገባል።

በእስራኤል እና ሐማስ መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ምክንያት፣ ዓለም አቀፍ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የኤፍ ቢ አይ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ አስታውቀዋል።

ባለፈው ጥቅምት በኦክላሆማ የሚኖር አንድ የአፍጋኒስታን ተወላጅ በአሜሪካ ምርጫ ወቅት ሕዝብ በብዛት የተሰበሰቡባቸውን ቦታዎች ለማጥቃት አሲሯል በሚል መያዙን ኤፍ ቢ አይ አስታውቋል።

በእ.አ.አ 2016 በኒስ፣ ፈረንሣይ የባስቲ ቀንን ለማክበር በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በመኪና ጥቃት ከተፈፀመ ወዲህ፣ በተሽከርካሪ የሚፈጸም ጥቃት በመላው ዓለም በተደጋጋሚ ተከስቷል።

ባለፈው ወር በጀርመን በተሽከርካሪ የተፈጸመውን የጅምላ ድንገተኛ ጥቃት ጨምሮ፣ ባለፉት ዓመታት በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቻይና፣ ስፔን፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ ተመሳሳይ ጥቃት በተሽከርካሪዎች ተፈጽሞ በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG