በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፈረንሳይ የኢትዮጵያን በውይይት የባሕር በር የማግኘት ጥረት ደገፈች


በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ በታደሰውንና አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ። ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም
በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ በታደሰውንና አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ። ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የነበሩት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ፣ ኢትዮጵያ በንግግር ፣ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና ጎረቤት ሀገራትን ባከበረ መልኩ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

ፕሬዝደንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ በመኾን በሰጡት መግለጫ በተያዘው የታኅሣሥ ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ቱርክ ላይ ለተፈረመው የአንካራ ስምምነት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።የሁሉንም ሉዓላዊነት ከማክበር ጋራ የተያያዘው ስምምነት ሊደገፍ የሚገባው እንደኾነም አክለዋል።

በቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ሸምጋይነት የተካሄደውን ሦስተኛ ዙር ድርድር ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግባቸውን ለመፍታት መስማማታቸው ይታወሳል።

መሪዎቹ አንዳቸው የሌላውን ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንደዚሁም ዓለም አቀፍ ሕጋዊ መርኾችን የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተርና የአፍሪካ ኅብረትን የመመስረቻ ሰነድ ለማክበር ያላቸውን ቁርጠኝነትም በስምምነቱ ወቅት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በቀጣዩ የካቲት ወር ቴክኒካዊ ድርድር ለመጀመርና በአራት ወራት ውሰጥ ለማጠናቀቅ መስማማታቸውም ተመልክቷል።

የአንካራው ስምምነት የተፈረመው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የቀድሞው የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ፣ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ከቀጠለው ውዝግብ በኋላ ነው።

የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን የአዲሰ አበባ ጉብኝት
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:28 0:00

እንደ ሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ገለጻ፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ የባሕር ጠረፍ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ቦታ ለ50 ዓመታት በሊዝ እንድትጠቀምና በምላሹም ለግዛቷ ዲፕሎማሲያዊ እውቅና እንድትሰጥ የሚያደርግ ነው።

ስምምነቱን ውድቅ ያደረገው የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን ጥሳለች ሲል ከሷል። የአንካራውን ስምምነት ያደነቁት ፕሬዝደንት ማክሮን፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እንዲሳካ ፈረንሳይ የበኩሏን ሚና መጫወት እንደምትፈልግ ጠቅሰዋል።

በንግግር፣ በውይይት፣ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ባከበረ መልኩና ጎረቤት ሀገራትን ባከበረ መልኩ መሠራት የሚቻልበትን መንገድ ሀገራቸው ለማመቻቸት እንደምትፈልግ አመልክተዋል ።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እ.አ.አ ታኅሣሥ 21 ቀን 2024 ዓ.ም አዲስ አበባ አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የአንድ ቀን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እ.አ.አ ታኅሣሥ 21 ቀን 2024 ዓ.ም አዲስ አበባ አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የአንድ ቀን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት በተመለከተ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ጋራ በዝርዝር መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር ማክሮንን ድጋፍ መጠየቃቸውና ፣ ፕሬዝደንቱም ጥያቄውን መቀበላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። "መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከፈረንሳይ እና ከፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ረገድ የሚጨበጥ ውጤት የሚጠብቅ መኾኑን ከወዲሁ ልገልጽ እፈልጋለሁ" በማለትም አክለዋል።

ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የነበሩት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕምድ አቀባበል ሲደረግላቸው።
ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የነበሩት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕምድ አቀባበል ሲደረግላቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፌስ ቡክ ገጽ ባሰፈረው መግለጫ "የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተ ረዥም ዘመን ለቆየው መሻት ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት ሁለቱ ወገኖች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል" ብሏል።

በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥትና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) መካከል በፕሪቶሪያ የተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት ምምነት በሁለቱ መሪዎች ውይይት ከተነሱት ነጥቦች አንዱ መኾኑን የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ገልጸዋል።

ሀገራቸው ከዚህ ስምምነት አተገባበር አንጻር ድጋፍ ማድረግ እንደምትፈልግም ጠቁመዋል። በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን በተለይም የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የኾኑ ሴቶችን መደገፍ ትፈልጋለች ብለዋል።

ከሽግግር ፍትህ ጋራ በተያያዘ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ማክሮን በአዲስ አበባ ቆይታቸው፣ በመንግሥታቸው የገንዘብ ድጋፍ የታደሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ወይም ኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ጎብኝተዋል።

ፈረንሳይ ለብሔራዊ ቤተመንግሥቱ እድሳት የ25 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓንም ተናግረዋል። ቤተመንግሥቱ የቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በ1948 ዓ.ም. የተገነባ ነው።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእድሳት ሥራም እንደዚሁ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ እየተካሄደ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስረድተዋል ።

በመጋቢት ወር 2012 ዓ/ም ኢትዮጵያን የጎበኙት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ሦስት አካባቢዎችን ባካተተው የአሁኑ ጉብኝታቸው የሀገራቸው ግዛት በኾነችው ማዬት እና በጎረቤት ጂቡቲ ቆይታ አድርገዋል። /ዘገባው ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል/

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG