የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ቡድኖች እና አጋር ሚሊሻዎች 20 ወራት ባለፉት የሱዳን ጦርነት፤ በደቡብ ሱዳን ሴቶች ላይ የጅምላ ጾታዊ ጥቃት ፈጽመዋል ሲል ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች ዛሬ ሰኞ በአወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ቡድን በዐዲሱ ሪፖርቱ ከጎርጎርሳዊያኑ መስከረም 2023 አንስቶ በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በቡድን መድፈር እና በጾታዊ ባርነት መያዝን ጨምሮ ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ከሰባት እስከ 50 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያሉ በርካታ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ መመዝገቡን አስታውቋል፡፡
ኒውርክ የሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ፣ ባለፈው ሳምንት በአወጣው ሌላ ሪፖርቱ፣ በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ከጎርጎርሳውያኑ ታኅሣሥ 2023 እስከ መጋቢት 2024 ድረስ ባለው ጊዜ፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና አጋር የአረብ ሚሊሻዎች በተለይም በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ኑባ ሲቪሎች ላይ ብዙ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን በስፋት ዘርዝሯል፡፡
"ጥቃቶቹ በስፋት ያልተዘገቡ" ናቸው ያለው መግለጫው "የጦርነት ወንጀሎች" ናቸው ብሏል፡፡
ባለፈው ጥቅምት የመንግሥታቱ ድርጅት ገለልተኛ ዓለም አቀፍ የሱዳን የሀቅ አጣሪ ተልዕኮ፤ ሁለቱም ወገኖች እንግልትና እና ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ በርካታ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ገልጿል።
"በሱዳን የመዘገብነው ጾታዊ ጥቃት መጠን እጅግ አስደንጋጭ ነው” ሲሉ የመርማሪ ቡድኑ ሰብሳቢ መሀመድ ቻንዴ ኦትማን ተናግረዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ የተባበሩት መንግሥታት ክትትል ውጤቱን "የማኅበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ" ሲል ውድቅ አድርጎታል፡፡
በቅርቡም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር፣ ሱዳን ውስጥ በወረርሽኝ መልክ በስፋት መፈጸሙን የገለጹት ጾታዊ ጥቃት በሴቶች ላይ ስለደረሰው ጾታዊ ጥቃት ወረርሽኝ ዓለም "የተሻለ ማድረግ አለባት" በማለት ሁኔታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዋች ባለፈው ሳምንት ባወጣው የመጀመሪያ ሪፖርቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ኅብረት “ሱዳን ውስጥ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት የሚጠብቅ ተልዕኮ በአስቸኳይ እንዲያሰማሩ” አሳስቧል።
መድረክ / ፎረም