የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ዛሬ እሁድ እንዳስታወቀው የታጠቁ ቡድኖች በቅርቡ የእርዳታ መኪኖችን በመዝረፋቸው ምክንያት፤ በጦርነቱ ወደ ተመሰቃቀለው የጋዛ ሰርጥ በዋናው የጭነት ማቋረጫ በኩል የሚደረገውን የእርዳታ ድጋፍ በስጋት ምክንያት እንደሚያቆም አስታውቋል። ተቋሙ እስራኤል በምትከተላቸው ፖሊሲዎች የተነሳ በአካባቢው የህግ እና የስርዓት መደፍረስ መኖሩን እንደ መንስዔ ጠቅሷል።
ውሳኔው ከቀዝቃዛው እና ዝናባማው የክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ በጋዛ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ሊያባብሰው ይችላል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በድንኳን መጠለያዎች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን በአለም አቀፍ የምግብ ዕርዳታ አቅርቦት ላይ ጥገኛ ናቸው። የእስራኤል ወታደሮች ከጥቅምት መግቢያ አንስቶ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለይተውት በቆዩት በግዛቱ ሰሜናዊ ክፍል ስላለው ረሃብ ባለሙያዎች አስቀድመው ሲያስጠነቅቁ ነበር።
በጋዛ ከፍተኛ የእርዳታ ድጋፍ ተደራሽ የሚያደርገው የመንግስታቱ ድርጅት የእርዳታ እና ሥራዎች ኤጀንሲ ዋና ሃላፊ ፊሊፔ
ላዛሪኒ በጋዛ በኩል ወደ ከሪም ሻሎም የሚወስደው መንገድ እጅግ አደገኛ ሆኗል ብለዋል። በነኅሴ ወር አጋማሽ ላይ ወደ ስፍራው ሲጓዙ የነበሩ 100 እርዳታ የጫኑ መኪኖች በታጠቁ ቡድኖች መዘረፋቸውን አስታውቀዋል። በተጨማሪም ትላንት ቅዳሜ የተደራጁ ቡድኖች አነስተኛ የምግብ መርከብ ዘርፈዋል ብለዋል።
ፊሊፔ ላዛሪኒ በኤክስ ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እስራኤል በጋዛ የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት ነች በማለት ከሰዋል።
በጉዳዩ ላይ ከእስራኤል ወገን የተሰጠ ምላሽ የለም።
መድረክ / ፎረም