የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በህዝብ መከላከያ ሃይሎች እና በቀድሞው የስለላ አዛዥ ጄኔራል አኮል ኩር ጠባቂዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት በሰላማዊ መንገድ የተፈታ ሲሆን፥ ሁለቱም ወገኖች ተጨማሪ ግጭት ላለመፍጠር ስምምነት ላይ ደርሰዋል በማለት አስታወቁ።
ሀሙስ ዕለት በጁባ ቶንግፒኒ በተሰኘው አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው የስለላ አዛዥ ኩር መኖሪያ ቤት ዙሪያ ለአንድ ሰዓት ያህል ከባድ የተኩስ ድምጽ የተሰማ ሲሆን፣ይህም በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ሽብር በመፍጠር በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግጭት ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት እንዲከስት ማድረጉ ተገልጿል።
የደቡብ ሱዳን ህዝብ መከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ሉል ሩአይ ኮዓንግ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የተኩስ ልውውጡ የተደረገው በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ትዕዛዝ መሰረት ኩር ወደ ሁለተኛ መኖሪያ ቤታቸው እንዲዛወሩ ለማድረግ በተወሰደው እርምጃ አለመግባባት ተከስቶ ነው ብለዋል።
የዜና አውታሮች ኩር ከስለላ አገልግሎት ከተሰናበቱበት ከጎሮጎሮሳውያኑ ጥቅምት 2024 መጀመሪያ አንስቶ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ ሲሉ ዘግበዋል። ይሁን እንጂ የደቡብ ሱዳን የመንግስት ባለስልጣናት የቀድሞው የስለላ አዛዥ በቁም እስር ላይ መሆናቸውን አስተባብለዋል።
ሰሞኑን በተከሰተው የተኩስ ልውውጥ የሁለት ወታደሮች ህይወት ሲያልፍ፤ ሁለት ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ በታጠቁ ተሽከርካሪ መገጨታቸውን ኮዓንግ አስታውቀዋል። አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ሰዎች ቆስለው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።
ኩር ከግጭቱ በኋላ በአንድ ከፍተኛ መኮንን ጥበቃ ስር ከባለቤታቸው፣ ከአንድ የግል ጠባቂ እንዲሁም ምግብ አብሳያቸው ጋር በመሆን ጀበል በተሰኘ አካባቢ ወደሚገኝ መኖሪያ ተዛውረዋል። ባለስልጣናት ሁኔታው ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበረ ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም