በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
ከ20 በላይ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ ቤተሰቦችና የመብት ድርጅት ገለጸ

ከ20 በላይ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ ቤተሰቦችና የመብት ድርጅት ገለጸ


የፍትህ ሚኒስቴር አርማ
የፍትህ ሚኒስቴር አርማ
 ከ20 በላይ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ ቤተሰቦችና የመብት ድርጅት ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:35 0:00

ሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋራ በተያያዘ፣ ታስረው ከነበሩ ከነበሩ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል 21 እስረኞች አኹንም በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ ጉዳያቸውን ሲከታተል የቆየው 'ሂዩማን ራይትስ ፈርስት’ የተባለ የመብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ።

የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች በበኩላቸው፣ ቤተሰቦቻቸው በምህረት እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው በኋላ፣ በመረጃ ስህተት ምክንያት ሊለቀቁ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። ፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የታሳሪዎቹ ጉዳይ በቅርቡ መታየት እንደሚጀምር አስታውቋል።

ዶር. ኢትባረክ ተፈሪ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በእስር ላይ ይገኛሉ ከተባሉት 21 ሰዎች መካከል አንዱ ጥቅምት 25፣ 2013 ዓ.ም የታሰሩት ወንድማቸው እንደሚገኙበት ገልፀው፣ በተያዘው የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት በምሕረት እንዲለቀቁ ውሳኔ አግኝተው እንደነበር ይናገራሉ።

ቃሊቲ የሚገኙ እስረኛ ወንድማቸውን ስም ቢጠቀስ ለወንድማቸው ደኅንነት እንደሚሰጉ የገለጹት፣ ድ.ር. ይትባረክ፣ በመረጃ ስሕተት ምክኒያት የምሕረቱ ተጠቃሚ አለመኾናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጉዑሽ ትርፈ ለ30 አመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል ሆኖ የሠራ ወንድማቸው፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተቀሰቀሰ ማግስት፣ ከሥራ ምድቡ ተይዞ መታሰሩንና ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወንድማቸው በአዲስ አበባ፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስሮ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ጉዑሽ፣ በይቅርታ እንዲፈታ ከተወሰነለት በኋላ፣ በመረጃ ስህተት ምክንያት አለመፈታቱን ጠቅሰዋል፡፡ ወደ ተለያዩ የፌደራል እና የክልል መስሪያ ቤቶች እየተመላለስን አመልክተናል የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ሆኖም እስካሁን ውጤት አልተገኘም ባይ ናቸው፡፡

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋራ ተያይዞ የታሰሩ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጉዳይን ላለፉት አራት አመታት ሲከታተል መቆየቱን የተናገረው ‘ሂዩማን ራይትስ ፈርስት’ የተባለ ኢትዮጵያዊ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ እስካሁን ያልተፈቱ ታሳሪዎች መኖራቸውን አስታውቋል።

የድርጅቱ ምክትል ዲሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለመጠይቅ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር በአዲሱ አመት መግቢያ ላይ፣ በርካታ ታሳሪዎችን በምህረት መልቀቁን አድንቀው፣ ሆኖም፣ አሁንም በምህረት ያልተለቀቁ መኖራውን በምርመራ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ስለዚህ ጉዳይ በአሜሪካ ድምፅ የተጠየቀው የፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የታሳሪዎቹ ጉዳይ በቅርቡ መታየት እንደሚጀምር አስታውቋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር የሚገኘው የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽ/ቤት፣ ኃላፊ ተወካይ ወይኒ ገብረሚካኤል፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ፣ “በቅርቡ ቦርዱ ሲሰበሰብ ጉዳያቸው ይታያል፣ ለቤተሰቦቻቸውም ይኸው መረጃ ተነግሯቸዋል” ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከመከላከያ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም፡፡ ቤተሰቦቻችን እስካሁን አልተፈቱም ካሉን አስተያየት ሰጪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ጉዑሽ ትርፈ፣ ስለ ኹኔታው ለማስረዳት ወደ ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፀጥታ ዘርፍ ፅ/ቤት ብንሔድም፣ ሰሚ አላገኘንም፣ በአግባቡም አልተስተናገድንም ብለዋል፡፡

በቅሬታው ዙርያ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ቃለአቀባይ አቶ ረዳኢ ሓለፎም አስተያየት ለማግኘት ብንጥርም፣ የእጅ ስልካቸው ስለማይነሳ ለዛሬ አልተሳካም፡፡ አቶ መብርሂ ብርሀነ በበኩላቸው፣ የታሳሪዎቹ ጉዳይ በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የ 2017 አዲስ አመትን አስመልክቶ ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ታይቶ እስከ ሞት ቅጣት የሚደርስ ፍርድ የተወሰነባቸው 178 የሰራዊት አባላት በምህረት እንዲለቀቁ መንግስት መወሰኑን አመልክቷል፡፡

/ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG