በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የናይል ተፋሰስ ሀገራት የግብፅን ድጋፍ ያላገኘው የውሃ ክፍፍል ስምምነት ተግባራዊ መሆኑን አስታወቁ


ፎቶ ፋይል፦ የዓሣ አጥማጆች ጀልባ በናይል ወንዝ ላይ እየተጓዘ በካይሮ፣ ግብፅ፣
ፎቶ ፋይል፦ የዓሣ አጥማጆች ጀልባ በናይል ወንዝ ላይ እየተጓዘ በካይሮ፣ ግብፅ፣

ከአባይ ወንዝ ተፋሰስ የሚገኘውን የውሃ ሀብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት፣ ከግብፅ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የአስሩ ሀገራት ቀጠናዊ አጋርነት አስታወቀ።

የናይል ተፋሰስ ተነሳሽነት እሁድ ዕለት በሰጠው መግለጫ ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ከተቀላቀለች በኋላ፣ የትብብሩ ማዕቀፍ ሕጋዊ ሁኔታ በአፍሪካ ኅብረት በይፋ ተረጋግጧል።

ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ታንዛኒያ ስምምነቱን አፅድቀዋል። ግብፅ እና ሱዳን ለመፈረም ፍቃደኛ ያልሆኑ ሲሆን ኮንጎ ድምጸ ተዕቅቦ አድርጋለች። ኬንያ እስካሁን የማፅደቂያ ሰነዶቿን ለአፍሪካ ህብረት አላስገባችም።

ከእሁድ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ስምምነት “የአባይን ወንዝ ለጋራ ተጠቃሚነት ለማዋል ፣ ፍትሃዊ እና ቀጣይነት ያለው ተጠቃሚነትን ለመጪ ትውልዶች ለማረጋገጥ ፣ ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው” ሲል የናይል ተፋሰስ ተነሳሽነት በመግለጫው አስፍሯል።

"ይህ ቅጽበት የናይል ተፋሰስ ሀገራት፣ መንግሥታት እና ህዝቦች እንዲሁም ሁሉም አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት ላሳዩት ትዕግሥት፣ እና የዓላማ ቁርጠኝነት ደስታችንን የምንገልጽበት ነው " ሲልም አክሏል ።

ስምምነቱ፣ በአባይ ውሃ ላይ ያላቸውን ድርሻ ለመቀነስ በሚደረጉ ማናቸውም ሙከራዎች ዙሪያ ስጋታቸውን ሲገልጹ በሰነበቱት በረሀማ ሀገራት፣ ግብጽ እና ሱዳን ሳይጸድቅ መቅረቱ የአወዛጋቢነቱ ማሳያ ሆኗል ።

ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ዋና ገባር በሆነው ጥቁር አባይ ላይ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ግድብ መገንባቷን በቀጠናው ውጥረት እንዲያይል አንድ ምክንያት ሆኗል ።

ኢትዮጵያ የግብጽን ፍላጎቶች ከግምት ውስጥ ካላስገባች ግድቡ የተፋሰስ ውሃ እና የመስኖ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ግብፅ ስጋት አላት። ኢትዮጵያ ግድቡን ተጠቅማ ሀገራዊ አንገብጋቢ ፍላጎት የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት አቅዳለች።

ስምምነቱ በመብት እና ግዴታዎች ዝርዝር ውስጥ የናይል ተፋሰስ ሀገራት "በየግዛቶቻቸው የናይል ወንዝን የውሃ ሀብት ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም አለባቸው" በሚል ደንግጓል።

6,695 ኪሎ ሜትሮች እርዝማኔ ያለው በዓለም ረጅሙ ወንዝ ናይል አንደኛው ገባሩ ከቪክቶሪያ ሀይቅ አዋሳኝ ቀጠናዎች የሚነሳው ነጭ አባይ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚነሳው ጥቁር አባይ ነው።

ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ፣ ግብፅ በቅርቡ ኢትዮጵያ በራስ ገዟ ሶማሊላንድ ግዛት በኩል የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ከተቃወመችው ከሶማሊያ ጋር የፀጥታ ትብብር ለማድረግ ቃል በመግባት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያላትን ስፍራ አጠናክራለች።

ባለፈው ሳምንት በተደረሰው ስምምነት መሰረት፣ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ስምሪት እ አ አ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ሲጠናቀቅ ፣ ግብፅ ሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ልታሰማራ ትችላለች።

አሁን በሥራ ላይ በዋለው የናይል ስምምነት ዙሪያ ከግብፅ አስተያየት ማግኘት እንዳልቻለ ሮይተርስ አክሎ ገልጿል። የናይል ተፋሰስ ተነሳሽነት መስራች አባል የሆነችው ግብጽ ፣ የአባይ ወንዝ ላይ መብቷ ፣ በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረሰው ስምምነት መሰረት እንዲጠበቅ ለረጅም ጊዜ ስትሟገት ቆይታለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG