በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከቤይሩት መውጫ አጥተው የድረሱልን ጥሪ የሚያሰሙት ኢትዮጵያውያን


ከቤይሩት መውጫ አጥተው የድረሱልን ጥሪ የሚያሰሙት ኢትዮጵያውያን
please wait

No media source currently available

0:00 0:10:58 0:00

እስራኤል የሄዝቦላህ ዋና መቀመጫ ናት ባለቻት ሊባኖስ ላይ የአየር ድብደባ ማካሄድ ከጀመረች ሁለት ሳምንታት ተቆጠሩ። ከቀናት በፊት ደግሞ እግረኛ ጦር በማስገባት ዘመቻዋን ቀጥላለች። በዚህ ጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ታዲያ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከሊባኖስ ለማስወጣት ስራ እንደሚጀምር ቢያስታውቅም፣ እስካሁን ከምዝገባ ውጪ የታየ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ መውደቃቸውን ኢትዮጵያኖቹ ገልጸዋል።

ሰላማዊት ግርማ ያለፉትን ስድስት አመታት የኖረችው ከሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በስተደቡብ በምትገኘው እና በብዛት የሺዓ ሙስሊሞች በሚኖሩባት ደሀዬ የተሰኘች ከተማ ነው።

ደሀዬ አሁን የእስራኤል ቦምብ የሚዘንብባት ከተማ ሆናለች። ከሁለት ሳምንት በፊት እስራእል በሄዝቦላህ ላይ በከፈተችው አዲስ ጥቃት ህንፃዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይርዋል። የከተማዋ ነዋሪዎችም ድንገት የደረሰውን ጥቃት ለመሸሽ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል። ሰላማዊት ጥቃቱ የተጀመረበትን የመጀመሪያ ቀን እንዲህ ታስታውሰዋለች።

"የመጀመሪያው ፍንዳታ ቀን የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰ ነበር የሚመስለው። ህንፃው እራሱ የተመታ ነበር የመሰለን። መሬት ወርደን ሁኔታውን ካወቅን በኃላ ተረጋጋን። ግን ማታውኑ የፅሁፍ መልዕክት ላኩ። በ500 ሜትር ርቀት ውስጥ የምትገኙ በሙሉ ውጡ አሉን። ለሊት ነው። የምንሄድበት የለንም። ያልተነጋገርሽውን፣ ያለተዘጋጀሽውን የትም መሄድ አትችይም። ስለዚህ ወጥተን ውጪ አደርን። ማታ ሦስት ሰዓት አካባቢ ነበር።"

ሰላማዊት ከቤቷ ስትወጣ ከለበሰችው ልብስ ውጪ ምንም አልያዘችም። ከዛን ቀን ጀምሮም የረባ እንቅልፍ አልተኛችም። ድንገት ጥላው የወጣችው መኖሪያ ቤቷ አሁን ባለበት ቦታ ይኑር ወይም አይኑር አታውቅም።

"ህይወታችንን ከዛ አካባቢ ከማውጣት በስተቀር ይዘን የወጣነው ነገር የለም። 24 ሰዓት የቀጠለ ድብደባ ስላለ ተመልሰን ሄደን የነበርንበት ቦታ እንዴት እንደሆነ፣ ምን እንዴት እንደሆነ ማየት የምንችልበት ሁኔታ የለም። ወደ እዛ ስለመሄድ ማሰብ እራሱ አልችልም።"

ያለፉትን አስር ቀናት መሰዋዕት የተሰኘ በሊባኖስ የሚንቀሳቀስ የኢትዮጵውያን ማህበር ባደረገላት ድጋፍ መቆየቷን የምትገልጸው ሰላማዊት በሊባኖስ የነበራት ኑሮ ያን ያክል የሰመረ አልነበረም። የሀገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ እና እ.አ.አ በ2020 በቤይሩት ወደብ ላይ የተከማቸ አልሞኒየም ናይትሬት ፈንድቶ ያስከተለው ከፍተኛ ጉዳት በኢኮኖሚው ላይ ያደረሰው ጫና ኑሮን ከእጅ ወደአፍ አድርጎባት ቆይቷል። በህይወቷ ግን እንደዚህ አይነት ከባድ ጊዜ አይታ እንደማታውቅ እንባ እየተናነቃት ትገልጻለች።

"በህይወቴ ይህን አይነት ከባድ ሁኔታ አይቼ አላውቅም። ማንም ሰው አያውቀውም። በጣም ከባድ ነው። ሰዎች ያለቅሳሉ። የምትቆሚበት መሬት እራሱ የሚመታ ነው የሚመስልሽ። እነሱ በጦርነት ከሚጋጠሟቸው ጋር በተያያዘ ሰዎች እንዲርቁ፣ እነሱ ባሉበት እንዳይቀመጡ ሲነገር እኛ ማን ምን ይሁን፣ የምንኖርበት ህንፃ ላይ ማን እንዳለ፣ የት እንደሆንን፣ እንዴት እንደሆነንን፣ ምን አናውቅም። የት መሄድ እናለብንና ምን ማድረግ እንዳለብን አናውቅም። በጣም ነው የተቸገርነው። የማዳም ቤት ልጆች አውጥተው ይጥሏቸዋል። ኤምባሲው ጋር በጣም ብዙ ሰው ነው ያለው። እኛም እዛ መሄ ፈልገን ነበር ግን እዛም ድምጹ በጣም ነው የሚረብሸው። ቦምብ በተመታ ቁጥር በጣም ይሰማል። ምክንያቱም ኤምባሲው ከደሀዬ ብዙም አይርቅም።"

ሰኞ መስከረም 13 ቀን እስራኤል ድንገት ማዝነብ በጀመረችው የቦምብ ናዳ ልክ እንደሰላማዊት ህይወት የተመሰቃቀለባቸው በመቶዎች እና በሺዎች የሞቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ነፍሳቸውን ለማዳን በየአቅጣጫው ተበታትነዋል። በሊባኖስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት የተወሰኑትን ቢያስጠልልም አብዛኞቹ መውጫ አጥተው ወይም በፍርሃት አደጋ ውስጥ እንዳሉ እኛ ለእኛ በስደት የተሰኘው ድርጅት መስራች እና መሪ ባንቺ ይመር ትገልጻለች።

"ሰው ቤት የሚኖሩ ከአሰሪዎቻቸው ጋር የተፈናቀሉ አሉ። አሰሪዎቻቸው በር ዘግተውባቸው ጥለዋቸው የሄዱ እና በቀይ መስቀል እና በተለያዩ ድርጅቶች እርዳታ የወጡ አሉ። በር ክፍት ሆኖም አሰሪዎቻቸው ጥለዋቸው የሄዱ ወይም በየኤጀንሲው ጥለዋቸው የሄዱ አሉ። መንገድ ላይም የተውዋቸው አሉ። በተጨማሪም ያለወረቀት ለአምስት አመት ሲንከራተቱ የነበሩ እህቶቻችንም ከየቦታው እየተፈናቀሉ ነው።"

ባንቺ እንደምትለው የሊባኖስ መንግስት በጥቃቱ ለተፈናቀሉ ዜጎቹ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመጠለያ ስፍራዎችን ቢያዘጋጅም፣ ስደተኞችን ግን አይቀበልም። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የውጪ ስደተኞች በተደራጁ የማህበረሰብ ተቋማት እና በግለሰቦች ብቻ እየተረዱ መሆናቸውን ትገልጻለች። እኛ ለእኛ በስደት የራሱ መጠለያ ባይኖረውም፣ ለኢትዮጵያንም ሆነ የሌሎች ሀገራት ዜጋ ስደተኞች ጊዜያዊ ድጋፎችን ይሰጣል።

"እንዴት እንደምገልጸው አላውቅም። በጣም ትልቅ ጭንቀት ውስጥ ነው ያሉት። ፍንጣሪ ያቆሰለው አለ። መንገድ ላይ ምጥ ይዟት የወለደች ኢትዮጵያዊት አለች። መንገድ ላይ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚሰማቸው ድንጋጤ እና ጭንቀት አለ። በተለይ ደግሞ እዚህ አካባቢ ልንመታ ነው ብለው የ15 ደቂቃ ወይም የ20 ደቂቃ መውጫ ጊዜ በሚሰጡበት ሰዓት፣ የሰው ቤት ሰራተኞች በአጠቃላይ መኪና የላቸውም። በዛ ቅፅበት ውስጥ ለመውጣት ያለው ጭንቀት፣ ያለው ፍራቻ በጣም የሚያሳዝን ነው። ምክንያቱም እነሱን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማውጣት የሚችል ቋሚ አካል የለም። በፀጥታው ስጋት ምክንያት እኛም መግባት የምንችልበት እና መግባት የማንችልበት ቦታ አለ።"

መሰዋዕት የተሰኘው የኢትዮጵያውያን ማህበርም ከደሀዬ ተፈናቅለው ወደ መሃል ሊባኖስ የሚመጡትን ኢትዮጵያውያን እየተቀበለ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው። ከማህበሩ አባላት መካከል አንዷ የሆነችው መላክ ኃይሌ ለተፈናቃዮቹ እርዳታ እያደረጉ ካሉ የሊባኖስ ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናት።

"አርብ እለት ብቻ አንዲት እህታችን 46 ልጆችን ተቀብላቸው ምግብ፣ አልባሳት፣ የሚተኙበት አዘጋጀንላቸው። ትላንትናም በጣም ብዙ ልጆች ተፈናቅለው መጥተው የምግብ እርዳታ እያደርግንላቸው ነበር። በእርግጥ ኤምባሲው መጠለያ ሰጥቶናል። ግን መጠለያው ቦንብ የሚጣልበት አካባቢ ቅርብ ስለሆነ አብዛኛዎቹ እዛ ለመግባት በጣም ይፈራሉ። ስለዚህ እኛ ወዳለንበት አካባቢ ይመጣሉ።"

መላክ የምትኖርበት መሃል ሊባኖስ ለጊዜው ሰላማዊ ይሁን እንጂ ነገ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው ፍርሃት ግን ሁሉም ጋር ተመሳሳይ ነው።

"በብዛት ሸዓ የሚባለው የሂዝቦላህ ደጋፊዎች ያሉበት ቦታ ነው የሚመታው። ወደ እኛ አካባቢ እስካሁን አልተመታም። ባይመታም ግን ፍርሃቱ እንዳለ ነው። ስራ ቆሟል። ሁሉም እርዳታ ጠባቂ ነው። ሁሉም ሰው ሀገሩ መግባት ነው የሚፈልገው። በቋፍ ነው ያለው። ትንሽ ኮሽ ባለች ቁጥር ሁሉም እያለቀሰ፣ እየፈራ፣ ዛሬ የት ነው የሚፈነዳው፣ ዛሬ እሞት እይሆን ወይ ብለው ደንግጠው ነው ያሉት። በጣም ነው የሚፈሩት።"


ከደሀዬ እምብዛም በማይረቀው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት የተጠለሉት ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ፍንዳታዎችን ይሰማሉ። ሰላማዊት ይህንን ድምፅ መቋቋም ባለመቻሏ ወደ መሃል ሊባኖስ ለመሄድ ተገዳለች። እዛም ሆና ግን ከአሁን አሁን እንደገና ሽሹ የሚል የፅሁፍ መልዕክት ሊመጣ ይችላል ብላ ስለምትፈራ እንቅልፍ እንደማይወስዳት ትናገራለች።

"እኔ ዛሬ ምግብ ቢያበሉኝ ፍርሃቴን ሊያስታግሱልኝ አይችሉም። በምናሳልፈው እያንዳንዱ ለሊት ነገን አይደለም የማስበው። ማደሬን፣ ጠዋት ነግቶ እራሴን ማግኘቴን ነው የማስበው። መንግስት እንዲደርስልን ነው የምንፈልገው በቃ።"

ሰላማዊትም ሆነች ሌሎች በቤይሩት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት ወደ ሀገራቸው መመለስ ነው። የኢትዮጵያ ቆንፅላ ፅ/ቤት ከሊባኖስ መውጣት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡ ባቀረበው ጥሪ መሰረትም ተመዝግባለች። እስካሁን ግን ምንም ነገር የለም።

"እኛ የኢትዮጵያ መንግስት ያስወጣን በቃ። ምንም ነገር ክፍያ እንዳይጠይቀን። ልብሳችንንም፣ ሻንጣችንንም፣ ምንም ማምጣት አንፈልግም። እራሳችንን፣ ነፍሳችንን ይዘን ከዚህ ሀገር መውጣት ነው የምንፈልገው። የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ከዚህ ህይወት፣ ከዚህ ሰቀቀን እንዲያወጣን ነው የምንፈልገው። እኔ እንቅልፍ ከተኛሁ አስር ቀን ሆኖኛል። ምክንያቱም መተኛት አንችልም። ይሄን ሰፈር ልቀቁ ወይም እንዲህ አድርጉ የሚሉ መልዕክቶች ይመጣሉ። ስለዚህ ያንን መከታተል አለብን። ቁጭ ብለን ያልገባንን እየጠየቅን ነው የምናድረው። በፍርሃት እና በሰቀቀን ነው ያለነው።"

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹ በአስቸኳይ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻች የምትጠይቀው ባንቺም፣ ያ እስከሚሆን ድረስ ኢትዮጵያውያን ሆኑ ሌሎች ስደተኞች መጠለያ እና ምግብ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች ትጠይቃለች።

እስራኤል በቤይሩት እና አካባቢዋ የምታደርገውን የአየር ጥቃት ቀጥላለች። ከፍተኛ ፍንዳታዎች የሚያስከትሉት ጭስ እና ነበልባልም ከየአቅጣጫው ይታያል። በየእለቱ የእናቴን እና የቤተሰቦቼን የጭንቀት የስልክ ጥሪ መመለስ አቅቶኛል የምትለው ሰላማዊት ደግሞ ከቤተሰቦቿ ጋር በሰላም የምትገናኝበትን ቀን በናፍቆት ትጠብቃለች።

XS
SM
MD
LG