በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ግብጽ በሳምንቱ መጨረሻ ወደሶማሊያ በድጋሚ የጦር መሣሪያዎች መላኳን በሚመለከት ያላትን ሥጋት ገለጸች


የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታየ አፅቀሥላሴ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታየ አፅቀሥላሴ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታየ አፅቀሥላሴ "የውጭ ኃይሎች ወደሶማሊያ የሚልኳቸው የጦር መሣሪያዎች አስቀድሞም ያለውን ደካማ የጸጥታ ሁኔታ ሊያባብሱ እና መሣሪያዎቹ በአሸባሪዎች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ" ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታየ ይህንን ሥጋታቸውን በኒው ዮርክ እየተካሄደ ካለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ከድርጅቱ የሰላም ግንባታ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሐፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ ጋር ባደረጉት ውይይት ያሳወቋቸው መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታየ ያሰሙትን ስጋት በተመለከተ ወዲያውኑ አስተያየት አልሰጠችበትም። ይሁን እንጂ የሶማሊያ የመከላከያ ሚንስትር አብዱልቃድር መሐመድ ኑር ከጦር ኃይሎች አዛዡ ከጄኔራል ኢብራሂም ሼክ ሙሄዲን ጋር ሆነው የጦር መሣሪያዎቹ የግብጽ ባንዲራ ካላት መርከብ ላይ ሲራገፉ ሲመለከቱ የሚያሳይ ፎቶ በፌስቡክ ገጻቸው አጋርተዋል።

የግብጽ መንግሥት ኢትዮጵያ ራሷን ከሶማሊያ ነጻ ሪፐብሊክ አድርጋ ካወጀችው ከሶማሊላንድ ጋር ካደረገችው አወዛጋቢ ውል ተያይዞ ቀጣናው ውጥረት ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ለሶማሊያ የጦር መሣሪያዎቹን መላኩን አረጋግጧል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ታሚም ኻላፍ ለሶማሊያ የተላኩት የጦር መሣሪያዎች ከትላንት በስተያ ዕሁድ ሞቃዲሾ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

ቃል አቀባዩ ባወጡት መግለጫ "ሶማሊያ ጸጥታዋን እና መረጋጋቷን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሽብርተኝነት ለመዋጋት ብሎም ሉዓላዊነቷን አንድነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት ግብጽ ትደግፋለች። በዚህም መሠረት የሶማሊያን የጦር ኅይል አቅም ለመገንባት የተላከው ወታደራዊ እርዳታ ዕሁድ ሞቃዲሾ ደርሷል" ብለዋል።

ሶማሊያ በቅርቡ ከግብጽ ጋር የመከላከያ ትብብር ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን አሁን ያለውን የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ሽግግር ተልዕኮ አትሚስን በሚተካው የሕብረቱ ተልዕኮ ውስጥ የግብጽ ወታደሮች እንዲሳተፉ ጋብዛለች። የኢትዮጵያ ወታደሮች እስከ መጪው ታሕሳስ ባለው ጊዜ ሀገሯን ለቅቀው እንዲወጡም ሶማሊያ ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታየ አፅቀሥላሴ በሚቀጥለው እአአ 2025 መጀመሪያ ላይ ሥራውን የሚጀምረውን አዲስ የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ አስመልክተው መናገራቸውንም የኢትዮጲያ የዜና አገልግሎት ዘገባው አመልክቷል።

'ማናቸውም የድህረ አትሚስ አደረጃጀት የሚኖረውን ሥልጣን፥ የሠራዊት መጠን፥ የፋይናንስ አቅርቦት እና ቅንጅት በሚመለከት አስፈላጊው ውይይት ተደርጎበት መወሰን እንዳለበት" ማሳሰባቸውን ዘገባው አውስቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG