በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ሊካሄድ የነበረው ሶስተኛው ዙር ውይይት ለሌላ ጊዜ ተላለፈ 


ፋይል፡ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳን ከኢትዮጵያና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጋር በመሆን መግለጫ ሲሰጡ፡፡
ፋይል፡ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳን ከኢትዮጵያና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጋር በመሆን መግለጫ ሲሰጡ፡፡

ውይይቱ ለሌላ ጊዜ የተላለፈው በኒውዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በመገጣጠሙ ምክንያት መሆኑን ሁለት የሶማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ስለጉዳዩ ለመገናኛ ብዙሃን ለመናገር ፈቃድ ስለሌላቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት አንደኛው የሶማሊያ ባለስልጣን የውይይቱ ጊዜ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጉዞ እና ዝግጅት ጋር መገጣጠሙ ተናግረዋል። ሁለተኛው ባለስልጣን በበኩላቸው ለውይይቱ ለመዘጋጀት ያለው ጊዜ "አጭር" እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ውይይቱ የፊታችን ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን ቱርክ አንካራ ላይ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ሲሆን መቼ እንደሚካሄድ አልተወሰነም፡፡ ነገር ግን ከተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ውይይቱ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ንግግሩ መራዘሙን በማስመልከት አስተያየት እንዲሰጡ ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።

ባለፉት ሀምሌ እና ነሃሴ ወራት በቱርክ ሸምጋይነት በአንካራ የተካሄዱት ሁለት ዙር ውይይቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ውጥረት ላይ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም።

አዲስ አበባ ከሶማሌላንድ ጋር የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ናቸው።

የሶማሌላንድ ባለስልጣናት እንደሚሉት በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ለመገንባት የሚያስችላት 20 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ወደብ ለ50 አመት በሚቆይ ሊዝ ታገኛለች። በምላሹ ለሶማሌላንድ እንደ ነጻ ሀገር እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ሀገር ትሆናለች። ሶማሊያ በበኩሏ ስምምነቱን ሉዓላዊነቷን እንደጣሰ አድርጋ ትመለከተዋለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG