ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ 100ሺህ የሚጠጉ ምጥን የኤምፖክስ ክትባቶች ዛሬ ሐሙስ እንደምትቀበል የአፍሪካ ህብረት ጤና ጥበቃ ተቋም አስታውቋል።
“ይህ የመጀመሪያ ክትባት ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመምጣቱ ደስተኞች ነን” ሲሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የተናገሩት የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ኃላፊ ዣን ካሴያ ኮንጎ ከ99 ሺህ በላይ ክትባቶች እንደምታገኝ አመልክተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በሀገሪቱ ከ17ሺህ 500 በላይ ሰዎች በኤምፖክስ በሽታ የተጠቁ ሲሆን፣ 629 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። ክትባቶቹ ከዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገን ተጭነው ዛሬ ኪንሻሳ አውሮፕላን ጣቢያ እንደሚገባ ተመልክቷል።
ለወረርሽኙ የሚሰጠውን ምላሽ እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው የኮንጎ ብሔራዊ የማህበረሰብ ጤና ተቋሙ ስለክትባቱ አመጣጥ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን የያዘውን ሰነድ ከአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ለማግኘት እየጠበቀ መሆኑንም የተቋሙ ዳይሬክተር አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኤምፖክስ ብሩንዲ፣ ኮንጎ ብራዛቪል እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን ጨምሮ ቢያንስ በ13 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደሚገኝ የአፍሪካ ጤና ማዕከል በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
መድረክ / ፎረም