ጅቡቲ "በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ጭቅጭቅ ሊፈታ የሚችል ሓሳብ አቅርባለች" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ዛሬ ቅዳሜ ከአሜሪካ ድምጽ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ከሚያዋስናት ድንበር በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የጅቡቲ ታጁራ ወደብ እንድትጠቀም ሀገራቸው ሃሳብ ማቅረቧን አስታውቀዋል።
የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስከትለው እኤአ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ፤ ኢትዮጵያ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊ ላንድ ግዛት የተፈራረመችውን እና ሶማሊያ ሉዓላዊነቴን የጣሰ ያለችውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ፤ ጅቡቲ እና ሌሎች እንደ ቱርክ ያሉ ሀገራት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት እና ቀውሱን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።
“ጅቡቲ አዲስ ወደብ ገንብታለች። በሰሜናዊ የጅቡቲ ክፍል የተገነባውን አዲሱን ወደብ ለማስረከብም ዝግጁ ናት” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አያይዘውም “ኮሪደሩ ቢያንስ የትራንስፖርት ወጭዋን በመቀነስ ኢትዮጵያን በእጅጉ ያግዛታል። ጅቡቲ በጋራ ወደቡን ከኢትዮጵያ ጋር የማስተዳደርን ሀሳብ ለመቃኘትም ዝግጁ ናት” ብለዋል።
ጅቡቲ ይህንኑ ሃሳቧን ለኢትዮጵያ መሪዎች ማስታወቋን ሚኒስትሩ አክለው አመልክተዋል።
ዩሱፍ አክለውም “በጉዳዩ አዎንታዊ ምላሽ አግኝተናል። የቀረበውን ሃሳብ በዝርዝር እየገመገሙት ነው። ስለዚህ በእርግጠኝነት በጥቂት ቀናት አሊያም ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በድጋሚ ተቀምጠን የመጨረሻውን ማስተካከያ የምናደርግ እና ያቀረብነው ሃሳብ የምናይ ይሆናል” ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ የባህር ኃይል ሰፈር ማቋቋምን እንደማያካትት ገልጸዋል ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በቱርክ ከሶማሊያ ጋር የተካሄደው ውይይት ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታየ አጽቀ ስላሴ “ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር ተጠቃሚነት ለማግኘት ያላት ህጋዊ ፍላጎት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ መንገድ በመተባበር” እንደሚሳካ እንደሚተማመኑ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጅቡቲ በቀረበው ሓሳብ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ የአሜሪካ ድምጽ ላቀረበው ጥያቄ ለጊዜው ምላሽ አልሰጠም።
መድረክ / ፎረም