ኢትዮጵያ፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይፋ ባደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ከዓለም የገንዘብ ተቋማት እና ከሌሎች ምንጮች በአጠቃላይ ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደ’ኤታው ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ መንግሥት፣ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ /ከግማሽ ትሪሊዮን በላይ /ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እንደሚጠይቅ፣ ሚኒስትር ደ’ኤታው ኢዮብ ተካልኝ ተናግረዋል።
በተያያዘ፣ የብር የመግዛት ዓቅም መዳከሙን ቀጥሎ፣ ባንኮች የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋን ከ100 ብር በላይ አድርሰዋል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች፣ የብር ዓቅም መዳከሙን እንደሚቀጥልና ሒደቱ በገበያው ላይ በሚኖረው የዶላር መጠን እንደሚወሰን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ፣ ሐምሌ 22 ቀን፣ ተግባራዊ ያደረገውን ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን ያካተተ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ፣ ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደ’ኤታ ኢዮብ ተካልኝ ተናግረዋል፡፡
ይህ ገንዘብ፣ ከዓለም የገንዘብ ተቋማት እና ከሌሎች ምንጮች በተለያየ መልክ የተገኘ እንደኾነም፣ ሚኒስትር ደ’ኤታው ከፋና ቴሌቪዥን ጋራ በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ፣ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በድጋፍ፣ በብድር እና በዕዳ ሽግሽግ በአጠቃላይ 16ነጥብ6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚለቅና ከዚኽም ውስጥ 1ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላሩን ማጽደቁን መግለጹ ይታወቃል፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(አይኤምኤፍ) ደግሞ በአራት ዓመት ውስጥ የሚለቀቅ 3ነጥብ4 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አጽድቋል፡፡
ከዚኽ ገንዘብ ውስጥ፣ መንግሥት፣ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የሚውል ተጨማሪ በጀት እንዲያጸድቅለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እንደሚጠይቅ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ባለፈው ሳምንት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስትር ደ’ኤታው ኢዮብ ተካልኝ ደግሞ፣ ተጨማሪው በጀት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ እንደኾነ ይፋ አድርገዋል፡፡
መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚወስዳቸው ርምጃዎች የሚኖራቸውን ተጽእኖ በአሉታዊ እና በአዎንታዊነት የሚመለከቱ ተንታኞች አሉ፡፡
መንግሥት ከሚወስደው የድጎማ እና መሰል ተግባራት ባለፈም፣ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ ማስታወቁ ይታወቃል፡፡
ይህን ተከትሎም፣ እስከ ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን ድረስ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከ2ሺሕ 200 በላይ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን፣ የንግድ ፈቃዳቸው የታገደና የተሰረዘ እንዲሁም ለእስር የተዳረጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን፣ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
ይህ ዐይነቱ ርምጃ “ችግሩን አይቀርፍም” የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው አቶ አማንይኹን ረዳ፣ ይልቁንም መንግሥት የገበያውን ክፍተት መሙላት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡
የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ፣ የብርን የመግዛት ዓቅም ወዲያውኑ በ30 በመቶ ያህል ያዳከሙት ባንኮች፣ በዚኹ ቀጥለው በዛሬው ዕለት የአንዱን ዶላር የመግዣ ዋጋ ከ100 ብር በላይ አድርሰዋል፡፡
ይኸው ሒደት እየዋዠቀ እንደሚቀጥል የሚጠቁሙት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው አቶ ክቡር ገና፣ በትይዩ ስለሚያሳድረው ጫናም ያብራራሉ፡፡
ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሞያው አቶ አማንይኹን ረዳ ደግሞ፣ ብር ከውጭ መገበያያ ገንዘቦች አንጻር ያለው ተመን፣ ወደ ኢትዮጵያ በሚገባው የውጭ ገንዘብ መጠን እየተወሰነ እንደሚቀጥል የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ በማንሣት ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት ደግሞ፣ ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከመሸጋገሩ በፊት፣ ባለፉት ዓመታት ምርትን በማሳደግና በሌሎችም ዘርፎች በቂ ዝግጅት መደረጉን ይገልጻል፡፡
በአንድ ወገን፣ ማሻሻያው “ከነፈተናዎቹም ጠቃሚ ነው” የሚሉ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ሲኖሩ፤ በአኳያው ደግሞ፣ በአገሪቱ ያለው የሰላም መደፍረስ ለምርታማነትም ይኹን ለኢንቨስትመንት ፈተና መኾኑን በመጥቀስ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ “አሁን ጊዜው አይደለም” በማለት የሚሞግቱም ባለሞያዎች አሉ፡፡
መድረክ / ፎረም