ዓለምን ከረሃብ ነፃ የማድረጉ ጥረት፣ በተለይም በድሃ ሃገራት በሚታዩት ቀውሶች ምክንያት ግስጋሴው እንደቆመና፤ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረትም ባለፉት 15 ዓመታት ጋሬጣ እንደገጠመው፣ ዛሬ ይፋ የሆነው ‘የዓለም የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ ሁኔታ’ ሪፖርት አስታውቋል።
‘የዘላቂ ልማት ግብ 2’፣ እንዲሁም ‘በ2030 ዜሮ ረሃብ’ የተሰኙ ግዙፍ የዓለማችንን ትልሞች ለማሳካት ብዙ እንደሚቀር፤ በተጨማሪም በቂ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ እየቀጠለ መሆኑን፣ በአምስት የተባበሩት መንግስታት ሥር ባሉ ድርጅቶች የተሠራው ጥናት አመልክቷል። ይህም በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በዓለም ጨምሮ የታየውን የረሃብ መጠን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ ጥናቱ ጠቁሟል።
ባለፈው ዓመት 733 ሚሊዮን ሰዎች በመላው ዓለም ረሃብ የገጠማቸው ሲሆን፣ ይህም በዓለም ከ11 ሰዎች አንዱ፣ በአፍሪካ ደግሞ ከአምስት ሰዎች አንዱ ማለት እንደሆነም ተመልክቷል።
“አሁን ባለው ሁኔታ፣ በ2030 በዓለም 582 ሚሊየን ሰዎች ለረሃብ ይጋለጣሉ፣ ከእነዚህም ውስጥ ግማሹ አፍሪካውያን ይሆናሉ” ሲሉ የፋኦ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ ማክሲሞ ቶሬሮ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል።
ይህም ሆኖ አንዳንድ አበረታች ምልክቶች እንደሚታዩና በቀጠናዎች መካከልም ሰፊ ልዩነት እንዳለ ቶሬሮ አመልክተዋል።
አፍሪካ ረሃብ በተጋረጠባቸው ሰዎች ብዛት ከፍተኛውን ድርሻ እንደምትይዝ፣ ይኽውም በመላው ዓለም ከሚገኙት ውስጥ 20 በመቶ እንደሆነ፤ በምግብ ዋስትና በኩልም በዓለም ከሚታየው እጥፍ፣ 58 በመቶ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም