ስደተኞቹ ወደ ዐዲሱ መጠለያ በመዛወር እንዲተባበሩ የስደተኞች ተቋሙ ጠየቀ
በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኘው የአውላላ የስደተኞች መጠለያ፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ታጣቂዎች ፈጸሙት በተባለ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቀ፡፡
በመጠለያው የሚኖሩ ስደተኞችም፣ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ባል እና ሚስት መኾናቸውን ጠቅሰው፣ “የአምስት ልጆች ወላጆች ነበሩ፤” ብለዋል፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው የመጠለያ ጣቢያው ጥበቃ ከተነሣ በኋላ መኾኑንም ስደተኞቹ አመልክተዋል።
ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር በበኩሉ፣ የጸጥታ ችግር አለባቸው የሚባሉትን የአውላላ እና የኩመር መጠለያዎችን በሒደት ለመዝጋት፣ ስደተኞቹን በዚያው ዞን ወደሚገኝ አፍጥጥ ወደሚባል ዐዲስ የመጠለያ ጣቢያ ማዛወር መጀመሩን ገልጿል።
የቅዳሜው ጥቃት የተፈጸመባቸውና ከሁለት ወራት በፊት ከአውላላ መጠለያ ለቀው መንገድ ዳር እየኖሩ ያሉት የሱዳን ስደተኞች በበኩላቸው፣ “ወደ ዐዲሱ የአፍጥጥ መጠለያ አንሔድም፤ የሚመለከታቸው አካላት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ ሦስተኛ ሀገር ያዛውሩን፤” ብለዋል።