ከሁለት መቶ በላይ ፍልሰተኞችን አሳፍሮ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በመጓዝ ላይ የነበረን ጀልባ በሃገሪቱ ባሕር ዳርቻ መያዟን ሴኔጋል አስታውቃለች።
ፍልሰተኞቹን ያሳፈረችው ጀልባ በሴኔጋል ሠራዊት ቃኚ ጀልባ የተያዘችው ላምፑል በመባል በሚታወቅ በሰሜን ምዕራብ በሚገኝ የዓሳ ማስገሪያ የባሕር አካል ላይ ሲሆን፣ አምስት ሴቶችን እና አንድ ታዳጊን ጨምሮ 202 ፍልሰተኞችን አሳፍራ አትላንቲክን ለማቋረጥ በመሞከር ላይ ነበረች።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ 170 ፍልሰተኞችን አሳፍራ ከሴኔጋል ተነስታ የነበረች ጀልባ ሞሪታኒያ ባሕር ዳርቻ ስትሰምጥ፣ 90 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አደጋውን ተከትሎ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ኡስማኔ ሶንኮ ሰዎች በባሕር ላይ ለማገልገል አቅም በሌለው ጀልባ ላይ ሆነው የአትላንቲክ ውቅያኖስን ማዕበል በመዳፈር ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ መክረውዋል።
በሜድትሬንያን ባሕር ላይ ባለው መሥመር ቁጥጥሩ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ፍልሰተኞች በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል ለመሻገር የሚያደጉት ሙከራ እየተበራከተ መጥቷል።
በስፔን የሚገኝ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሚለው፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ብቻ ከ5 ሺሕ በላይ ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
መድረክ / ፎረም