በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ ውድመን በተባለ ስፍራ፣ በመከላከያ ኀይል እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ባለፈው ሳምንት ዐርብ መካሔዱ በተገለጸው የተኩስ ልውውጥ፣ ስድስት ያልታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን፣ የሟች ቤተሰብ እና የአካባቢው ነዋሪ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
ከሟቾቹ ውስጥ አምስቱ የቅርብ ዝምድና እንዳላቸው አስተያየት ሰጭዎቹ ጠቅሰው፣ ከእነርሱም ሦስቱ አባት እና ልጅ መኾናቸውን አመልክተዋል፡፡
የጉባላፍቶ ወረዳ አስተዳደር፣ የደረሰውን ጉዳት አምኖ መጠኑን ግን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ ሻለቃ ያሬድ አባተ፣ “ከመንግሥት በተቃራኒ የቆሙ” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፣ በሕዝቡ መሀል ሳሉ የተኩስ ልውውጥ ስለሚደረግ ባልታጠቁ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡