በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም መሪዎች የግድያ ሙከራውን በማውገዝ ላይ ናቸው


የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት እና የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ፣ ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በፔንሰልቬኒያ፣ ባትለር ውስጥ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ የምርጫ ቅስቀሳ ያደርጉበት ከነበረው መድረክ እንዲወርዱ በሰዎች ሲረዱ/ ፎቶ/ ኤፒ
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት እና የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ፣ ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በፔንሰልቬኒያ፣ ባትለር ውስጥ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ የምርጫ ቅስቀሳ ያደርጉበት ከነበረው መድረክ እንዲወርዱ በሰዎች ሲረዱ/ ፎቶ/ ኤፒ

የዓለም መሪዎች የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ላይ ሳሉ በተሰነዘረባቸው የግድያ ሙከራ በጥይት ተመትተው መቁሰላቸው እጅግ እንዳስደነገጣቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።

ከዓለም ዙሪያ ፕሬዝደንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች በፖለቲካ የተነሳሳ ጥቃትን በማውገዝ በጥቃቱ ለተጎዱ ሰዎች ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ከአውሮፓ የአውሮፓ ኮሚሽን ኡርሱላ ቮን ዴር ሌየን የደረሰው ጥቃት " እጅግ እንዳስደነገጣቸው" ገልጸው "በፖለቲካ የተነሳሳ ጥቃት በዲሞክራሲ ቦታ የለውም" ብለዋል። "አስጸያፊ ተግባር" ያሉት የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሹልዝ ዲሞክራሲ ላይ ስጋት የሚደቅን ብለው አውግዘዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮን በበኩላቸው "በዲሞክራሲዎቻችን የተሰነዘረ አሳዛኝ ጥቃት" ብለው " የአሜሪካን ህዝብ ድንጋጤ እና ቁጣ እኛም እንጋራለን" ብለዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስ የጥላቻ ቅስቀሳ ፖሊሲዎቿን ልትገመግም ይገባል" ያለችው ሩሲያ አጋጣሚውን ዋሽንግተን ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማውገዝ ተጠቅማበታለች።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ " ምናልባት ገንዘቡ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሕግ እና ሥርዐት ለሚያስከብሩ የፖሊስ እና ሌላም አገልግሎቶች ቢውል ሳይሻል አይቀርም" ማለታቸው ተጠቅሷል።

የዩክሬይን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው ጥቃቱ እጅግ እንዳስደነገጣቸው እና ትረምፕ ፈጥነው እንዲያገግሙ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የቻይና ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ በሚስተር ትረምፕ ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸዋል። የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትርም " በወዳጄ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በጥልቅ አሳስቦኛል" ካሉ በኋላ "በዲሞክራሲያው ሀገር በፖለቲካ ጉዳይ ጥቃት ቦታ የለውም" ብለዋል።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳም "ዲሞክራሲ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃትን በአንድ ላይ አጥብቀን መቃመም አለብን" ማለታቸው ተጠቅሷል። የታይዋን ፕሬዝደንትም በጥቃቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

ከመካከለኛው ምስራቅ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጥቃቱ እጅግ እንዳስደነገጣቸው ገልጸው ለትረምፕ ደህንነት እና ቶሎ ማገገም ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

ጥቃቱን "የክህደት ተግባር" ሲሉ የጠሩት የግብጽ ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በበኩላቸው የዩናይትድ ስቴትስ የምርጫ ዘመቻዎች የሽብር የሁከት እና የጥላቻ ተግባር በሌለበት በሰላማዊ እና በጤናማ መንገድ እንዲቀጥሉ ምኞቴን እገልጻለሁ" ብለዋል። የአርጀንቲና፥ የብራዚል፥ የቺሌ፥ የቦሊቪያ እና የኮሎምቢያ መሪዎችም የግድያ ሙከራውን አውግዘዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG