በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ተፋላሚዎች የተኩስ አቁም ለማድረግ እየተደራደሩ ነው


ሱዳን ግንቦት 2015
ሱዳን ግንቦት 2015

የመንግስታቱ ድርጅት በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ቡድኖች በጄኔቫ ሚሊዮኖችን ባፈናቀለው ግጭት የሲቪሎችን ደህነንት ለማስጠበቅ፣ የእርዳታ አቅርቦቶች ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ እና በተኩስ አቁም ዙሪያ ለሁለተኛ ቀን መወያየታቸውን አስታውቋል።

ውይይቱ ሐሙስ ዕለት ቋጥኝ በሚያክል ተግዳሮት ተጀምሯል ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት የጄኔቫ ቃል አቀባይ አሌሳንድራ ቬሉቺ በዕለቱ ከሁለቱ ተወያዮች መካከል የአንደኛው ወገን ተወካይ ሳይገኙ መቅረታቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የትኛው ወገን ሳይገኝ እንደቀረ ከመናገር ተቆጥበዋል።

ቃል አቀባይዋ “ሁለቱ አካላት መወያየታቸውን ማረጋገጥ እሻለሁ” ያሉ ሲሆን “የትኛው ተፋላሚ ፓርቲ በስፍራው ሳይገኝ እንደቀረ ዝርዝሩን ግን ልሰጣችሁ አልችልም፤ ልነግራችሁ የምችለው ነገር በዛሬው ዕለት ውይይቱ መቀጠሉን ነው” ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።

ቃል አቀባይዋ የሱዳን የሁለቱ ወገን ተወካዮች በአካል ተገናኝተው ከመወያየት ይልቅ ‘ፕሮክሲሚቲ ቶክ’ ተብሎ በሚጠራውና ሁለቱ ተወካዮች በተለያዩ ስፍራዎች ሆነው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ የግል ልዑክ የሆኑት ራምቴን ላማምራ በሁለቱ መካከል እየተመላለሱ በማወያየት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቬሉቺ አክለውም ከ15 ወራት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ድርድሩ በአንድ ቀን መዘግየቱ እምብዛም መሰረታዊ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

በሱዳን ጦርነቱ ከጀመረበት ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም አንስቶ 19 ሺህ ሰዎች ሲሞቱ 33 ሺህ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት አመላክቷል። የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶችም 12.7 ሚሊየን ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ሌሎች 10.5 ሚሊየን ሰዎች በሀሪቱ ውስጥ መቅረታቸውን እንዲሁም 2.2 ሚሊየን ሰዎች በአምስት የጎረቤት ሀገራት በስደት ላይ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ቬሉቺ ድርድሩ እስከመቼ ድርስ እንደሚዘለቅ ግልጽ አይደለም ሲሉም አክለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG