ተወዳጁ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ ደራሲ እና የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነቢይ መኰንን፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በሞት መለየቱን፣ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል አስታውቋል፡፡
ባደረበት ሕመም ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ በዛሬው ዕለት ከረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ በመኖሪያ ቤቱ ያረፈው ኹለገቡ የሥነ ጽሑፍ ባለሞያ ነቢይ መኰንን፣ ከመሥራቾች አንዱ ኾኖ በዋና አዘጋጅነት በሠራባት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ መለያ አሻራዎቹን አሳርፏል።
ወግ ዐዋቂው ነቢይ፣ ባህል እና ጥበብ ለአገራዊ ለውጥ ኹነኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በጽኑ እንደሚያምንየሚገልጹት ባልደረቦቹ፣ በልዩነት የሚታወቅበትን ሳምንታዊ ርእሰ አንቀጽ፣ በተረት እና ምሳሌ ከመጻፍ ጀምሮ፣ ጋዜጣዋ በጥበብ እና ባህል ላይ አተኩራ እንድትሠራ ማድረጉን ይናገራሉ።
ዝነኛው ገጣሚ ነቢይ፣ ተከታታይ የግጥም መድበሎች ጸሓፊ ብቻ አይደለም፡፡ ወጣት ገጣምያንና ጸሓፍት በአዲስ አድማስ ላይ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ሰፊ መድረክ በማመቻቸት፥ ተተኪ ጸሐፍት፣ ደራስያንና ገጣምያን እንዲፈሩም አስችሏል፡፡ ከእነርሱም፣ መጻሕፍትን በማሳተም ለመታወቅ የበቁ ደራስያንና ገጣምያን ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ነቢይ፣ ዝነኛ የተውኔት እና ድራማ ጸሐፊም ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለእይታ አብቅቷል፤ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ፣ ራሱ ነቢይ መኰንንና ሌሎችም አርቲስቶች ተውነውበታል፡፡ በድጋሚም ቀርቦ በከፍተኛ አድናቆት ታይቷል፡፡ “ናትናኤል ጠቢቡ” የተሰኘ ተውኔትም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል፡፡ “ጁሊየስ ቄሳር”፣ ሌላው ተርጉሞ ለእይታ ያበቃው ተውኔት ነው፡፡
በመጻሕፍት በኩል፣ “Gone with The Wind” የተሰኘውን የማርጋሬት ሚሼል የአሜሪካ ክላሲክ መጽሐፍ፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርእስ የተረጎመበት ዳጎስ ያለ መጽሐፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጨረሻ ለኅትመት የበቃው ይኸው መጽሐፉ፣ በደርግ መንግሥት በማዕከላዊ ታስሮ በነበረበት ወቅት፣ በሲጋራ ወረቀት ላይ እየተረጎመ በድብቅ በማስወጣት በመጨረሻ ሲፈታ ያሳተመው ነው፡፡ ነቢይ መኰንን፣ ይህን የእስር ጊዜውን በተመለከተ፣ ከሸገር ኤፍኤም 102.1 ራዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም አዘጋጇ መዓዛ ብሩ ጋራ ባደረገው ረዘም ያለ ተከታታይ ቃለ ምልልስ በስፋት አውግቶታል።
ሌላው መጽሐፉ፣ ከፍተኛ ተነባቢነትን የተቀዳጀው “የኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው ነው፡፡ በአሜሪካ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ ሦስተኛው መጽሐፉ ደግሞ፣ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲኾን፣ “The Last Lecture” ከሚለው መጽሐፍ የተመለሰ ነው፡፡ “ስውር ስፌት” ቁጥር አንድ እና ሁለት፣ “ነጭ ግራጫ” የተሰኙና ሌሎችም ያልታተሙ በርካታ ሥራዎች አሉት፡፡
የሦስቱ መጻሕፍት ምረቃ በቅርቡ በተከናወነበት መድረክ ላይ፣ ኹለገቡ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነቢይ መኰንን፣ የሕይወት ታሪኩን ጽፎ እንደጨረሰና ለአርትዖት በወዳጆቹ እጅ እንደሚገኝ ተገልጾ ነበር፡፡
በቀድሞ ናዝሬት በአሁኑ አጠራሯ አዳማ ከተማ የተወለደውና የዐፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት ፍሬ የኾነው ገጣሚውና ኹለገቡ የሥነ ጽሑፍ ሰው ነቢይ መኰንን፣ በችሎታውም ኾነ በታዋቂነቱ የማይታበይና የማይኮፈስ፣ ይልቁንም ለቀረቡት ኹሉ ደግነቱ እና ቅንነቱ ልዩ እንደነበር፣ ወዳጆቹ እና የሥራ ባልደረቦቹ በከፍተኛ ስሜት ይመሰክሩለታል፡፡
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ አብሮት በመሥራት ጠቃሚ ክህሎት ማትረፉን የሚናገረው ባልደረባው ኢዮብ ካሳ፣ “በቅርበት የማውቀው የልብ ወዳጄ ነቢይ መኰንን በደግነት የተትረፈረፈ ነበር፤” ይላል - ድንገተኛ ኅልፈቱን አስመልክቶ ባሰፈረው ማስታወሻው፡፡ “አንድም ቀን አለቃዬ መስሎ ተሰምቶኝ አያውቅም፤ ስለ ጋዜጣ አሠራር፣ ስለ አርትዖት፣ ስለ አጻጻፍ ስለ ግጥም፣ ስለ ትርጉም ሥራ ወዘተ… ከእርሱ ተምሬአለኹ፤” በማለትም የልብ ወዳጅነቱን ገልጿል፡፡
ይኸው ባልደረባው አያይዞም፣ ነቢይ፥ በደርግ ዘመን በኢሕአፓ አባልነቱ ፀረ አብዮተኛ ተብሎ በማዕከላዊ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን ቢያይም፣ ከሞት መንጋጋ በተረፈበት እስራቱ የማይሞቀው የማይበርደው፣ ኀዘኑም ደስታውም የተመጠነ ሰው እንደነበር ገልጿል፡፡ በእስራቱ ዘመኑ ከማማረር ይልቅ፣ እርሱ እና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ኾነ ክፉ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍ እና ከመናገር ቦዝኖ እንደማያውቅም አስታውሷል፡፡
“ሐሳብን አይፈራም፡፡ ለሕዝብ እና ለአገር የሚጠቅም አንዳች ሐሳብ ያላቸው ወገኖች ኹሉ፣ እንዲጽፉ ሲያበረታታና ሲደግፍ ኖሯል፤” በማለትም ያክላል፡፡
በተወለደ በ68 ዓመቱ ያረፈው ገጣሚ፣ ተርጓሚ እና ደራሲ ነቢይ መኰንን፣ ባለትዳር እና የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ነው፡፡
የቀብር ሥነ ሥርዐቱ፦ ነገ፣ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ረፋድ አራት ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር የአስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር ከተከናወነ በኋላ፣ የቀብር ሥነ ሥርዐቱ፣ ከቀኑ በ7:00 በአዳማ ከተማ እንደሚፈጸም ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም