በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በናይጄሪያ የአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ሞቱ


በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምሥራቅ ቦርኖ ግዛት
በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምሥራቅ ቦርኖ ግዛት

በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምሥራቅ ቦርኖ ግዛት፣ ትላንት ቅዳሜ፣ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ሴት አጥፍቶ ጠፊዎች ፈጽመውታል በተባለ ተከታታይ ጥቃት፣ ቢያንስ 18 ሰዎች ሲገደሉ፣ 30 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የአካባቢው የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ ተናግረዋል።

ቦርኖ፣ ለ15 ዓመታት በዘለቀው የእስላማዊ ዐማፅያን ቡድኖች ጥቃት፣ ሰዎች በሺሕዎች የተገደሉበትና በሚሊዮኖች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉባት ቦታ ነው። የናይጄሪያ ጦር፣ የታጣቂዎቹን ዐቅም ቢያጣጥለውም፣ አሁንም በሰላማዊ ሰዎች እና በጸጥታ ዒላማዎች ላይ ገዳይ ጥቃቶች እየደረሱ ናቸው።

የቦርኖ ግዛት የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዲሬክተር ባርኪንዶ ሳኢዱ እንዳሉት፣ አጥፍቶ ጠፊዎች በግዎዛ ከተማ እንዳደረሷቸው በተጠረጠሩ የተናጠል ጥቃቶች፣ በሠርግ፣ በቀብር ሥነ ሥርዓት እና በሆስፒታል በርካታ ሰዎችን ገድለዋል፤ ብዙዎችንም አቁስለዋል።

በዓይነቱም በመጠኑም ዘግናኝ ነው በተባለው በዚኹ ጥቃት፣ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የገለጹት አቶ ሳኢዱ፣ ከተጎጂዎቹም ሕፃናት፣ ጎልማሶች እና ነፍሰ ጡር እናቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የቦርኖ ግዛት ፖሊስ አስተያየት ለመስጠት ወዲያውኑ አልተገኘም።

ቦኮ ሃራም እና የተከፋፈለው እስላማዊ ቡድን፣ አየርላንድን በምታኽለው ሰፊዋ ገጠራማ የምዕራብ አፍሪካ ቦርኖ ግዛት ውስጥ፣ በጣም ንቁ ተዋጊ ቡድኖች መኾናቸው ይነገራል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG