እየጨምረ የመጣውን የኮሌራ ወረርሽኝ ጨምሮ በርካታ የጤና ቀውሶችን እያስተዳንገደች በምትገኘው አፍሪካ ውስጥ ክትባቶችን ለማምረት የዓለም መሪዎች፣ የጤና ቡድኖች እና የመድኃኒት ኩባንያዎች የ1.2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
ፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው የሕክምና ጉባዔ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአፍሪካ የክትባት ማምረቻን ለማስጀመር የሚደረገው ጥረት "ሀቀኛ የአፍሪካ ገበያን ለማቋቋም የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ይሆናል" ብለዋል።
ማክሮን አክለው ከገንዘብ ድጋፉ ሦስት አራተኛ የሚሆነው ከአውሮፓ እንደሚገኝ፣ ከቦትስዋና፣ ከሩዋንዳ፣ ከሴኔጋል እና ከጋና የተወከሉ መሪዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ሚኒስትሮች፣ የጤና ቡድኖች እና የመድሃኒት አምራቾች በተገኙበት ጉባዔ ላይ ተናግረዋል።
ጀርመን ለዚህ እቅድ 318 ቢሊየን ዶላር እንደምታዋጣም የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በቪዲዮ አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።
ፈረንሳይ ለእቅዱ 100 ሚሊየን ዶላር የምታዋጣ ሲሆን እንግሊዝ 60 ሚሊየን ዶላር ትሰጣለች። እንደ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ ጃፓን እና ጌትስ ፋውንዴሽን የመሳሰሉትም ድጋፍ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።
እቅዱ "በአፍሪካ ውስጥ የመድሃኒት ኢንዱስትሪን ለማበረታታት እና በአባል ሀገራት መካከል ትብብር ለመፍጠር ያስችላል" ሲሉ በጉባኤው ላይ የተናገሩት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት አፍሪካ 99 ከመቶ የሚሆነውን ክትባት በከፍተኛ ውጪ ከውጪ እንደምታስገባ ጠቅሰዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ክትባት ስርጭት ዙሪያ የሚታየውን ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍል ይፋ ያወጣ ሲሆን፣ ትላልቅ የመድሃኒት አምራች ተቋማት ያሏቸው ሀብታም ሀገራት አብዛኛውን ክትባት መውሰዳቸው አፍሪካን ወደኃላ አስቀርቷታል።
በቅርቡ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ያገረሸው የኮሌራ በሽታ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ክትባት አምራቾች እንደሚያስፈልጉ አጉልቶ ያሳየ ቢሆንም እስካሁን በዓለም ላይ ለበሽታው የሚሆን ርካሽ እና ውጤታማ ክትባት የሚያመርተው፣ የደቡብ ኮሪያው ኢዩ-ባኢኦሎጊክስ የተሰኘ አንድ ድርጅት ብቻ ነው።
ኮሌራ ግማሹን የአፍሪካ ክፍል እያጠቃ መሆኑን ያመለከቱት ማክሮን፣ ባዮቫክ የተሰኘው የደቡብ አፍሪካ መድሃኒት አምራች ኩባንያ የኮሌራ ክትባቶችን ማምረት እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም