በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን ጦርነት ልጆች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አሳሳቢ መኾኑን ተመድ አስታወቀ


ከሱዳን ጀዚራ ግዛት የተፈናቀሉ ሰዎች በተፈናቃዮች በታጨቀ መኪና ወደ ምስራቃዊቷ ሱዳን ገዳረፍ ከተማ መግቢያ ሲደርሱ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም
ከሱዳን ጀዚራ ግዛት የተፈናቀሉ ሰዎች በተፈናቃዮች በታጨቀ መኪና ወደ ምስራቃዊቷ ሱዳን ገዳረፍ ከተማ መግቢያ ሲደርሱ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

ጦርነት ላይ ባለችው ሱዳን ልጆች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከሁሉም በቀዳሚነት የሚያስጨንቃቸው መኾኑን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጦርነት የተጠመዱ ሕጻናት ልዑክ ተናገሩ።

ከሱዳን ቀጥሎ የኮንጎ እና የሄይቲ ሕጻናት ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ቨርጂኒያ ጋምባ አስታውቀዋል።በዓለም ዙሪያ ግጭቶች በሚካሄዱባቸው ሥፍራዎች ልጆች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚመለከቱ ሪፖርቶችን የማቅረብ ኃላፊነት ያላቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣኗ ይህን ያሉት የዋና ጸሐፊው ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ጋዜጣዊ ጉባዔ ላይ ነው።

ልዩ ልዑኳ በሕጻናት ላይ ጥቃት በመፈጸም የተፈረጁ ወገኖችን የሚዘረዝረውን ሪፖርት ጠቅሰው ወደ አጎራባች ባንግላዴሽ እየተዛመተ ባለው በሚያንማር የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ሕጻናት ያሉበት ሁኔታ ሌላው ስጋታቸው መሆኑን አውስተዋል። የሶማሊያ እና የአፍጋኒስታን ሕጻናት አስጊ ወደሚሆንበት ደረጃ እያመራ መሆኑንም አንስተዋል።

የተመድ ሪፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ የእስራኤል ኃይሎችን፥ ሃማስን እና የፍልስጥዔም እስላማዊ ጂሃድ ተዋጊዎችን አብሮ በ2023 የሕጻናት መብት ጣሾች መዝገብ ውስጥ አስገብቷቸዋል። ሃማስ በደቡባዊ እስራኤል ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት ሲሆን የእስራኤል ኃይሎች ደግሞ የሃማስን ጥቃት ለመበቀል ጋዛ ውስጥከሚያካሂዱት መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት በተያያዘ የሕጻናትን መብት የሚጥሱ ዝርዝር ውስጥ ተፈርጀዋል።

በዩክሬይን ጦርነት ውስጥ የተጠመዱት ሕጻናትም ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ሪፖርቱ ያወሳ ሲሆን የሩሲያን ኃይሎች ለሁለት ዓመታት በተከታታይ በሕጻናት መብት ጥሰት አድራሾች ዝርዝር ከትቷቸዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ልዩ ተጠሪዋ ቨርጂኒያ ጋምባ " ከሁሉም በላይ ለዚህ ዓመትም ሆነ ለሚመጣው ዓመት የሚያሳስበኝ በሱዳን ያለው በተለይም የዳርፉር ጉዳይ ነው። ጦርነቱ እየተስፋፋ በመሆኑ የቻድ ሁኔታም ያሳስበኛል" ማለታቸውን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ ጠቅሷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG