የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ ባሪያ ፍንገላ ሥርአት ማክተሙ የተበሰረበትን ቀን መታሰቢያ እንዲሆን በማድረግ በየዓመቱ በፊዴራል ደረጃ የሚከበረውን ጁንቲንዝ በሚል ሥያሜ የሚወቀውን በዓል ምክንያት በማድረግ ትናንት ሰኞ ምሽት በዋይት ሐውስ ቅጥር ጊቢ ከሚገኘው መስክ ላይ የሙዚቃ ድግስ መስተንግዶ አድርገዋል።
በዝግጅቱ ላይ በመንፈሳዊ ዜማዎቹ የሚታወቀው ከርክ ፍራንክሊን መድረኩ ላይ ከምክትል ፕሬዚደን ሀሪስ ጋር የደነሰ ሲሆን፤ ዝነኞቹ ፓቲ ላ ቤልን እና ቻርሊ ዊልሰንን ጨምሮ ሙዚቃዎቻቸውን ተጫውተዋል።
ባይደን በሥነ ስርአቱ ወቅት ባሰሙት ንግግር አዲስ ልብስ የለበሱ "አንዳንድ አሮጌ መናፍስት" ጥቁር አሜሪካውያን በብርቱ ትግል ያገኟቸውን መብቶች ሊነጥቁዋቸው ተነስተዋል’ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የትናንቱ የዋይት ሀውስ ቤተ መንግሥት ‘የጁንቲንዝ’ ዝግጅት የተካሄደው በጆ ባይደን እና በሪፐብሊካኑ ዕጩ በዶናልድ ትረምፕ መካከል በሚደረገው የበረታ ፉክክር የጥቁር አሜሪካዊያን መራጮች ድምጽ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው እየተገለጸ ባለበት በዚህ ወቅት ነው።
ፕሬዝደንት ባይደን በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር በየዓመቱ ሰኔ 19ኝን የፌዴራል መንግሥት በዓል ያደረገውን ሕግ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2021 መፈረማቸው ይታወሳል።
መድረክ / ፎረም