በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች


ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:44 0:00

በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ልዑክ (አትሚስ) የሥራ ዘመኑ በመጪው ታህሳስ በሚያበቃበት ጊዜ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ወታደሮች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እንደሚጠበቅ የሶማሊያ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አስታውቀዋል።

አማካሪው ሁሴን ሼክ አሊ በቅርቡ በሃገሪቱ ብሔራዊ የመገናኛ አውታሮች እንዳስተላለፉት መልዕክት ከሆነ፣ በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ በመዋቀር ላይ ባለው አዲስ የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደሮች አይካተቱም። አዲሱ ልዑክም በእ.አ.አ 2025 ለአንድ ዓመት እንደሚያገለግል አስታውቀዋል።

የፀጥታ አማካሪው አስተያየት የመጣው የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ ለቆ መውጣት የአል ሻባብ ነውጠኞችን የሚጠቅም እንደሚሆን የአገሪቱ አንዳንድ ክልላዊ ባለሥልጣናት በመናገር ላይ ባሉበት ወቅት ነው።

ሁሴን ሼክ አሊ ጨምረው እንዳሉት፣ ውሳኔው በኢትዮጵያና በራስ ገዟ ሶማሌላንድ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ የወደብ

አገልግሎትና የባሕር ኃይልን በተመለከተ ላደርጉት የመግባቢያ ስምምነት የተሰጠ ምላሽ ነው።

ስምምነቱ ሉአላዊነቷን የሚጋፋ እንደሆነ በመግለጽ ሶማሊያ ተቃውማለች፡፡

“የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎችን በተመለከተ ያለን አቋም ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ ሉአላዊነታችንን፣ ድንበራችንን እና የፖለቲካ ነፃነታችንን መጣሷን እስከቀጠለች ድረስ፣ ሰላምና ደህንነትን ለማምጣት በምናደርገው ጥረት ውስጥ እንደ አጋር ልናያት አንችልም” ሲሉ ሁሴን ሼክ አሊ በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ መልዕክታቸውን አስፍረዋል።

ሁሴን ሼክ አሊ ለሮይተርስ በተጨማሪ እንዳሉት፣ “የያዝነው የሰኔ ወር ከማለቁ በፊት ወይም የልዑኩ የሥራ ግዜ ከመጠናቀቁ በፊት የመግባቢያ ስምምምነቱ የማይሻር ከሆነ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ወታደሮች ሃገሪቱ ለቀው መውጣት አለባቸው” ብለዋል።

የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኦማር በበኩላቸው “አሁን እንደሚታየው የፖለቲካ ድባብ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ አካል መሆን አይችልም” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሺሕ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ይገኛሉ፡፡ ሶስት ሺሕ የሚሆኑት በአፍሪካ የሽግግር ልዑክ ውስጥ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ከአምስት እስከ ሰባት ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ በሁለቱ ሃገራት የፀጥታ ስምምነት መሠረት የተሰማሩ ናቸው።

XS
SM
MD
LG