በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አቶ የሸዋስ አሰፋ ታሰሩ


የቀድሞው የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ
የቀድሞው የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ
አቶ የሺዋስ አሰፋ ታሰሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:12 0:00

የቀድሞው የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ ታሰሩ። የፓርቲው የቀድሞ አመራር አባል ናትናኤል መኮንን ደግሞ ከእስር ተለቀቁ። “የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ” በሚል መሪ ቃል ላለፈው ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠርቶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ ከነበሩት ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት የቀድሞው የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ ፣ ዐርብ ግንቦት 23 /2016 ዓ.ም ምሽት ላይ መታሰራቸውን የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

አቶ የሺዋስ “ዐርብ ዕለት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ከባለቤቱ እና ከሁለት ልጆቻቸው ጋራ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመግባት ላይ እያሉ ፣ የአዲስ አበባ የደኅንነት አባላት መሆናቸውን በገለፁለት ሲቪል የለበሱ ሰዎች በተለምዶ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደሚባለው፣ የቀድሞው ማዕከላዊ፣ ተውስዷል” ሲሉ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ኹኔታውን ለአሜሪካ ድምፅ አስረድተዋል፡፡

በምን ጉዳይ ተጠርጥሮ እንደተያዘ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ መሆኑ ይታወቃል፣ በወቅታዊ ጉዳይ ትፈለጋለህ” ብለው ነው የያዙት በማለት መልሰዋል፡፡

አቶ የሺዋስ አሰፋን የያዙት “የደኅንነት አባላት” በወቅቱ የፍርድ ቤት መጥሪያ እንዳልያዙ እና በዛሬው እለት ደግሞ መኖሪያ ቤቱን ፈትሸው፣ “ለምርመራ እንፈልጋቸዋለን” ያሏቸውን ሰነዶችና ሌሎች ቁሶች ይዘው እንደሔዱም መጋቢ ቢሉይ አብርሃም ተናግረዋል፡፡

የአቶ የሺዋስን መታሰር በተመለከተ ከአዲስ አበባ ፖሊስ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት፣ የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ስልክ ባለመመለሳቸው አልተሳካልንም፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ለህዳር 30 ተጠርቶ ከተሰረዘው ሰላማዊ ሰልፍ ጋራ በተገናኘ ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞው የኢዜማ አመራር አባል ናትናኤል መኮንን፣ 6 ወር ለሚጠጋ ጊዜ በአዋሽ አርባ ከታሰሩ በኋላ ደግሞ ዛሬ መለቀቃቸውን መጋቢ ቢሉይ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ አቶ ናትናኤል ተለቀው ወደ ቤታቸው መግባታቸውን እንዳረጋገጡ እና በስልክ እንዳናገሯቸውም ገልፀዋል፡፡

ከሰላማዊ ሰልፉ ጋራ በተገናኘ ኅዳር 27 በቁጥጥር ስር ከዋሉት አራት አስተባባሪዎች ውስጥ፣ መጋቢ ቢሉይ አብርሃምን ጨምሮ አራት ሦስቱ ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የሰልፉ አስተባባሪ መሆናቸውን በይፋ በፊርማቸው ካረጋገጡ 13 ፖለቲከኞች መካከል መጋቢት 17 ቀን በፖሊስ የተያዙትን የኢሕአፓ ሊቀመንበር ረ/ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራን ጨምሮ አራት ግለሰቦች. እንዲሁም ፊርማቸው ካልሰፈረ አስተባባሪዎች ውስጥ ናቸው ያሏቸው ሌላ አንድ ግለሰብ ደግሞ አሁንም በአዋሽ አርባ ታስረው እንደሚገኙ መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ገልፀዋል፡፡

የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ያቀዱ 97 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል” ብሎ ነበር፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች “የአማራ ክልል ጽንፈኛ ኃይሎች እና የሸኔ የሽብር ቡድን” ብሎ ከገለጻቸው ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ከመጠቆም ውጭ፣ መግለጫው ማንነታቸውን በይፋ አላሳወቀም፡፡

ይሁንና፣ በሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት አራት አባላቱ መታሰራቸውን ኅዳር 28 ቀን የገለጸው የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ፣ በዕለቱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ “የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአስተባባሪዎቹ እና በማኅበረሰቡ ላይ ከሰልፉ ጋራ በተገናኘ ወከባ እየፈፀሙ መኾናቸው አስግቶናል” በማለት ሰልፉ እንዲሰረዝ መወሰኑን በወቅቱ አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG