በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በግጭቶች መቀጠል የዐያሌ ኢትዮጵያውያን የጤና አገልግሎት መታጎሉን ቀይ መስቀል ገለጸ


በግጭቶች መቀጠል የዐያሌ ኢትዮጵያውያን የጤና አገልግሎት መታጎሉን ቀይ መስቀል ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:05 0:00

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በቀጠሉ የትጥቅ ግጭቶች ምክንያት የጤና አገልግሎቶች ክፉኛ መስተጓጎላቸውን፣ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በምኅጻሩ አይሲአርሲ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቶቹ፣ በተለይም በገጠር እና በሩቅ አካባቢዎች የጤና አገልግሎቶች ላይ ክፉኛ ተጽእኖ ማሳደራቸውንና መድኃኒቶችን ለማቅረብም አዳጋች እንደኾነበት አመልክቷል፡፡

ኮሚቴው በማኅበራዊ የትስስር ገጾቹ ባጋራው መግለጫው፣ “ቁስለኞች፣ ሕሙማን፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች፣ በጤና አገልግሎቱ ለተፈጠረው ችግር ዋና ተጋላጮች ናቸው፤” ብሏል።

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቃል አቀባይ ሮቢን ዋውዶ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በተለይም በዐማራ ክልል የቀጠለው አለመረጋጋት፣ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶችን ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

“በጸጥታው መደፍረስ የተነሣ በግጭት አካባቢዎች ባሉ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች እና ሌሎች የሕክምና ማዕከላት መድኃኒትን ማድረስ ከባድ ኾኗል፤” የሚሉት ቃል አቀባዩ፣ አንዳንድ ጊዜም፣ በመንግሥት ኀይሎች እና መንግሥትን በሚዋጉ ቡድኖች የሚጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችም ተጽእኖ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ግጭት የቀጠለባቸውን የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች በምሳሌነት ያነሡት ቃል አቀባዩ፣ ሲቪሎች በቀላሉ መንቀሳቀስ ባይችሉም እንደ ሰብአዊ ድርጅት፣ የምንችለውን ያህል ለመሥራት እየሞከርን እንገኛለን፤ ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አሳሳቢነቱን የገለጹት ሌላው የግጭት አካባቢዎች ኹኔታ፣ የሪፈራል ሥርዓትን ነው፡፡ ይህም፣ ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳይችል እያደረገው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የሪፈራል ሥርዓት፣ በከፍተኛ ባለሞያዎች ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችን ለመከባከብ የሚያስፈልግ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ወደ መጀመሪያ ደረጃ የጤና ማዕከል የሚሔድ ታካሚ፣ ሕክምናውን በዚያ ማግኘት ካልቻለ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የሕክምና ባለሞያዎች ወዳሉበት የተሻለ ሆስፒታል ይላካል፡፡ ኾኖም፣ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች አንዳንዴ ታካሚዎች በተጻፈላቸው ሪፈራል መሠረት፣ ከአንድ የጤና ማዕከል ወደ ሌላው ሔደው የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና ማግኘት አይችሉም፤ ይላሉ፡፡

ኮሚቴው፣ በአስቸጋሪ ኹኔታም ውስጥ፣ በጣም የተጎዱ ማኅበረሰቦች ባሉባቸው የግጭት ቀጣናዎች አንዳንድ የሕክምና ችግሮችን ለማቃለል፣ የሕክምና ተቋማትን በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። በምንገኝበት የአውሮፓውያኑ 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ100 በላይ የጤና ተቋማት የተለያዩ ድጋፎች ሲደረግላቸው፣ ከእነዚህም መካከል 62ቱ በዐማራ ክልል፣ 17ቱ በኦሮሚያ ክልል፣ 20 በትግራይ ክልል እና 6 በሶማሌ ክልል እንዳሉ አመልክቷል፡፡

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋትን በማክበር ለተቸገሩት የሕክምና ርዳታ ሳይስተጓጎል መቅረብ እንዲችል፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ ካሉ ኀይሎች ጋራ በመደበኛነት ንግግር እያደረገ እንደሚገኝም በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ሮቢን ዋውዶ ስለሚደረጉት ንግግሮች ለአሜሪካ ድምፅ ሲያብራሩ፣ “በውጊያው ከሚሳተፉት ሁለቱም አካላት ጋራ የሰብአዊ አገልግሎቶችን ኹኔታ በተመለከተ እያነሣን ውይይት እናደርጋለን፤” ብለዋል፡፡

የሰብአዊ ቡድኖቻችን ድጋፍ ወደሚፈልጉ ስፍራዎች ሲንቀሳቀሱ፣ ታጣቂ ቡድኖች የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጡን እየተነጋገሩ መኾኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ ውይይቱ የመንግሥት ባለሥልጣናትንም የሚያካትት፣ “ምስጢራዊ እና የሁለትዮሽ ነው፤” ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ፣ የሲቪሎችን ደኅንነት መጠበቅን በተመለከተም፣ ከመንግሥት እና ከታጣቂ ቡድኖች ጋራ እየተነጋገሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም፣ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት “የሲቪል ተቋማት ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ እስረኞች፣ ቁስለኞች እና ሕሙማን ጥበቃ እና ክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው በውይይቶቹ ላይ እንደሚነሣ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቃል አቀባይ ሮቢን ዋውዶ አክለው አመልክተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG