በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች


በኢትዮጵያ ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ዩናይትድ ስቴትስ ጠየቀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:53 0:00

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪን ጄ.ማሲንጋ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ አገራቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያላትን ፖሊሲ የሚያንጸባርቅ ንግግር አድርገዋል፡፡ አምባሳደሩ፣ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ግቢ ባደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያ በትጥቅ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት፣ ግጭት አቁመው በንግግር ሰላምን እንዲያሰፍኑና የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ አሳስበዋል፡፡

የታጠቁ ቡድኖች፣ ፖለቲካዊ ዓላማዎቻቸውን በዐመፅ ለማሳካት እየገፉ መኾናቸውንና መንግሥትም ይህን ለመከላከል የሚወስዳቸው ርምጃዎች፣ በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ የማይካድ ተጽእኖ ያለው መኾኑን የተናገሩት አምባሳደር ማሲንጋ፣ ውይይትን ወደ ጎን ያለው ይህ አካሔድ የመብት ጥሰቶችም እንዲቀጥሉ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በመላ አገሪቱ “ሰላማዊ ዜጎች፣ በተለያዩ ኀይሎች ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ አስገዳጅ ስወራ፣ ከግጭት ጋራ የተያያዘ ጾታዊ ጥቃት እና ሌሎችም ጥቃቶች እየተፈጸሙባቸው መኾኑን የሚገልጹ ዘገባዎችን ስናይ እጅግ አዝነናል፤” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች፣ እውነተኛ እና ግልጽ የሽግግር ፍትሕ ሒደትን በመሰለ የተጠያቂነት አሠራር በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል፤ ያሉት አምባሳደሩ፣ ለታጣቂዎች እና ለመንግሥት በየስማቸው እየለዩ ቀጥተኛ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች፣ ፊታቸውን ወደ ድርድር እንዲያዞሩ አምባሳደሩ ሲጠይቁ፤ ህወሓት፣ በኀይል ወሰን ለማስመለስ ከሚደረግ እንቅስቃሴ እንዲቆጠብና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም የሰላም ውይይትን እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕከክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ልዩ ልዩ የሲቪክ ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች እና ተወካዮች በተገኙበት አምባሳደሩ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በውስጣዊ ግጭቶች እየታመሰች እንደምትገኝ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ የአገሪቱን ችግሮች በኀይል ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት እንዲቆጠብ የጠየቁት አምባሳደሩ፣ በእስር ላይ የሚገኙ ቁልፍ የፖለቲካ ሰዎችን መፍታቱ ጠቃሚ እንደኾነም

አስገንዝበዋል። ያን ተፈጻሚ ማድረግም፣ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉትን የፖለቲካ ውይይት ሊያግዝ እንደሚችል ነው የተናገሩት።

አምባሳደር ማሲንጋ፣ ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈጸምም ጠይቀዋል፡፡

ሁሉም የታጠቁ ተዋናዮች፣ በመላ አገሪቱ ዐዲስ የሕዝብ መፈናቀልን ጨምሮ ለሰዎች ሥቃይ ምክንያት ከመኾን መገታት እንዳለባቸው ያነሡት አምባሳደሩ፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትንና የውኃ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረግ እንዲቆም፣ የተሟላና ያልተገደበ ሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህም እንደ መነሻ፣ ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁምን እንደሚጨምር አመልክተዋል፡፡

ግጭት የኢትዮጵያውያንን ሥቃይ ከማባባስ ያለፈ መፍትሔ የሌለው በመኾኑ፣ ውይይት ትኩረት እንዲደረግበት ያሳሰቡት አምባሳደሩ፣ ምንም እንኳን ፍጹም ሊኾን ባይችልም፣ ኹሉም ወገኖች የአገራዊ ምክክሩን ዕድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በአምባሳደሩ ንግግር ላይ፣ ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ወዲያውኑ የተሰጠ ምላሽ እና አስተያየት የለም፡፡ ምላሽ ካገኘን በሌላ ዘገባ ይዘን እንመለሳለን፡፡

XS
SM
MD
LG