በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሳማ ኩላሊት የተተካላቸው የመጀመሪያው ታካሚ በሁለት ወራቸው ሞቱ


የአሳማ ኩላሊት ህክምና (ፎቶ አሶሴይትድ ፕሬስ)
የአሳማ ኩላሊት ህክምና (ፎቶ አሶሴይትድ ፕሬስ)

የተሻሻለ የአሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው በህይወት የነበሩት የመጀመሪያው ታካሚ ህክምናው ከተደረገላቸው ከሁለት ወራት በኋላ ህይወታቸው ማለፉን ህክምናውን ያከናወነው የአሜሪካ ሆስፒታል ገለጸ።

የቦስተን ማሳቹሴትስ ጀኔራል ሆስፒታል ቅዳሜ ረፋዱ ላይ በሰጠው መግለጫ "ሆስፒታሉ በሚስተር ሪክ ስሌመን ድንገተኛ ህልፈት በጣም አዝኗል። ህልፈታቸው በቅርቡ ከተደረገው የንቅለ ተከላ ውጤት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ግን ምንም ፍንጭ የለንም" ብሏል።

በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በማሳቹሴትስ አጠቃላይ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሃኪሞች ባለፈው መጋቢት፣ የመጨረሻው አስከፊ ደረጃ ነው በተባለው የኩላሊት ህመም ይሰቃዩ ለነበሩት የ62 ዓመቱ ስሌመን የተሳካ የንቅለ ተከላ ህክምና አድርገው እንደነበር ተገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ ባወጣው መግለጫ “ስሌመን በመላው ዓለም መተኪያ ለሚሹ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ህሙማን የሁል ጊዜ ተስፋ ሆነው ይኖራሉ፣ ዜኖትራስፕላንቴሽን ለተባለው የንቀለ ተከላ እምነትና ፈቃዳቸውን በመስጠት ለህክምናው መዘመን ላደረጉት አስተዋጽኦ ከልባችን እናመሰግናቸዋለን” ብሏል፡፡

በስኳር በሽታ እና የደም ግፊት ሲሰቃዩ የኖሩት ስሌመን እኤአ በ2018 የሰው ኩላሊት የተተካላቸው ቢሆንም ኩላሊቱ ከአምስት ዓመታት በኋላ አገልግሎት መስጠት ማቆሙ ተጠቅሷል፡፡

ሆስፒታሉ በመጋቢት ወር የተሳካ ንቅለ ተከላ መደረጉን ሲያበስር ስሌመን በሂደቱ መስማማታቸውን ተናግረው፣ ህክምናው ለሳቸው ብቻ ሳይሆን “በሕይወት ለመትረፍ ንቅለ ተከላ ለሚያስፈልጋቸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋ የሚሰጥ ነው” ብለው ነበር።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እስካለፈው መጋቢት ወር ድረስ ከ89000 በላይ የኩላሊት ህሙማን ተተኪ ኩላሊት ለማግኘት ተመዝገበው እየተጠባበቁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በየቀኑ በአማካይ 17 ሰዎች እንደሚሞቱ ተመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG