በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መንግሥት የብዙኀን መገናኛ ዐዋጁን እንዲያከብር ባለሞያዎች ጠየቁ


መንግሥት የብዙኀን መገናኛ ዐዋጁን እንዲያከብር ባለሞያዎች ጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:59 0:00

የኢትዮጵያ መንግሥት የብዙኀን መገናኛ ዐዋጁን እንዲያከብርና እንዲያስከብር፣ የዓለም የፕሬስ ወርን ለማክበር አዲስ አበባ ላይ የተሰባሰቡ ባለሞያዎች ጠየቁ። የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እና ዩኔስኮ፣ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ወርን ለመዘከር፣ ዛሬ ዐርብ፣ ግንቦት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ በትብብር ባዘጋጁት ውይይት ላይ፣ መንግሥት የወጡትን ሕጎች እና ዐዋጆች እንዲያከብር በባለሞያዎች ተጠይቋል።

በሌላ በኩል፣ በዐዋጁ ላይ የተቀመጡ መብቶችን በማክበር እና በማስከበር በኩል የሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮች እንዲቀረፉ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን፣ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት ገልጿል።

የዘንድሮው “የፕሬስ ነጻነት ቀን” በኢትዮጵያ እየተከበረ ያለው፣ የአገሪቱ የፕሬስ ነጻነት ደረጃ እያሽቆለቆለ እንደሚገኝ እየተገለጸ ባለበት ወቅት ነው፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት በ2011 ዓ.ም. “ጋዜጠኞች በእስር ቤት የማይገኙባት፣ በዘርፉ ብዙ መሻሻል ያሳየች” በሚል ተወድሳ፣ ዓለም አቀፉን የፕሬስ ነጻነት ቀን ክብረ በዓል ያስተናገደችው ኢትዮጵያ፣ ከዚያ በኋላ ከዓመት ዓመት ደረጃዋ በየጊዜው እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ በመረጃ ነጻነት መብት ላይ የሚሠራው “ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ” የተባለ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፣ ዘንድሮ ምዘና ከተደረገላቸው 180 ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ 141ኛ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ኃላፊ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ዶር. ጌታቸው ድንቁ፣ ለፕሬስ ነጻነት ማሽቆልቆል፣ በአገሪቱ የተፈጠሩ ግጭቶችንና የፖለቲካ አለመረጋጋቶችን በዋና ምክንያትነት አንሥተዋል፡፡

ከፖለቲካ ቀውሶች በተጨማሪ፣ ጽንፍ የያዙ የተለያዩ አካላት ፍላጎቶች እና ሌሎችም ምክንያቶች፣ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ላይ ተጽእኗቸው እየበረታ እንደኾነ የሚገልጸው፣ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የዜና እና ወቅታዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ሪፖርተር ኤርሚያስ በጋሻው፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዲሬክተር መስዑድ ገበየሁ፣ መንግሥት የብዙኀን መገናኛ ዐዋጁን ማክበር እና ማስከበር እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ጫናዎችን ለመቋቋም፣ የብዙኀን መገናኛ ተቋማት በጋራ ድምፃቸውን ማሰማት እንዳለባቸውም ይመክራሉ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል ታምራት ኀይሉ፣ በዐዋጁ ላይ የተቀመጡ መብቶችን በማክበር እና በማስከበር በኩል የሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮች እንዲቀረፉ ለማድረግ ምክር ቤቱ እየጣረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ከመንግሥት በኩል ምላሽ እና አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት፣ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣናት ስልክ ባለመመለሳቸው ሊሳካልን አልቻለም፡፡

ከፕሬስ ነጻነት ማሽቆልቆል ጋራ በተገናኘ የሚቀርቡበትን ክሶች በተደጋጋሚ የሚያስተባብለው መንግሥት፣ በእስር ላይ የሚገኙ የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎች፣ በሥራቸው ምክንያት ሳይኾን በሽብር እና ሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ እንደኾኑ በመግለጽ ይከላከላል፡፡ ይኹንና ባለሞያዎቹ በወንጀል ቢጠረጠሩም “በጋዜጠኝነት ሥራቸው ነው” በማለት፣ የጋዜጠኞች እና ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የመንግሥትን ምክንያት ይቃወማሉ፡፡

XS
SM
MD
LG