ዩክሬን ከሩሲያ ወረራ ወዲህ ሶስተኛውን ፋሲካ በምታከብርበት በዛሬው ዕለት፣ ሩሲያ በርካታ ድሮኖችን አስወንጭፋ ወታደሮቿ አንድ ኢላማ ሲያደርጉት የቆየን መንደር ተቆጣጥረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ የዛሬውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሕዝባቸው “በአንድ የጋራ ፀሎት እንዲያደርስ” ጠይቀው፣ ከሩሲያ ጋራ በሚያደርጉት ጦርነት “አጋራቸው” እግዚያብሔር አምላክ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ሩሲያ ሻሂድ 24 ድሮኖችን አስወንጭፋ፣ 23 ተመተው እንደወረዱ የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል። በካርኪቭ ክልል በደረሰው ጥቃት አንድ ሕፃንን ጨምሮ ቢያንስ 16 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል።
ከሰማይ የተመቱት ድሮኖች በሕንፃዎች ላይ ሲወድቁ እሳት መከሰቱም ተነግሯል።
ኦቸረቲና የተሰኘውን እና በዶነትስክ ክልል የሚገኘውን መንደር ወታደሮቿ እንደተቆጣጠሩ ሩሲያ አስታውቃለች፡፡
በመዲናዋ ኪቭ፣ ምዕመናን የዛሬውን የፋሲካ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከቤታቸው ሆነው በኢነተርኔት እንዲከታተሉ ባለሥልጣናት አሳስበዋል።
“በእንዲህ ዓይነቱም ቀን ቢሆን፣ ከወራሪው በኩል ሰይጣናዊ ድርጊት ሊፈጸም ይችላል” ሲሉ የከተማው አስተዳዳሪ አስጠንቅቀዋል።
መድረክ / ፎረም