በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለፋሲካ በዓል የሃይማኖት አባቶች የሰላም እና የእርቅ ጥሪ አስተላልፈዋል


ለፋሲካ በዓል የሃይማኖት አባቶች የሰላም እና የእርቅ ጥሪ አስተላልፈዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:13:03 0:00

የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤን በዓል በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኙትን፣ የተራቡትን፣ የተጠሙትን እና የታረዙትን በማሰብ፣ በማገዝ እና በማጽናናት እንዲያሳልፉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ እና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያናት አባቶች ጠይቀዋል። "እንደ ክርስቲያኖች መኖር እንጀምር" ያሉት የሃይማኖት አባቶች፣ ጥላቻ እና መከፋፋት እንዲቀር፣ በምትኩ በመግባባት እና በመወያየት የፖለቲካ እርቅ እንዲመጣ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እና ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የትንሳኤን በዓል የሚያከብሩት ዛሬ ነው።

እለቱ እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ከመቃብር የተነሳበት ቀን የሚታሰብበት በዓል ሲሆን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ በዓል ተደርጎ እንደሚቆጠር የሃይማኖት አባቶች ያስረዳሉ።

የበዓሉ አከባበር የሚጀምረውም ከፋሲካ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ዘምባባ በማሰር ከሚከበረው የሆሳዕና እሁድ ሲሆን ይህ ሳምንት በምን መልኩ እንዳለፈ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አባ ኤርሚያስ ያስርዱናል።

ከፋሲካ ቀደም ብሎ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ለ55 ቀናት፣ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ደግሞ ለ40 ቀናት የሚፆመው የሁዳዴ ጾም ማገባደጃ የሆነው የሕማማት ሳምንት በካቶሊክ ቤተክርስቲያንም እንዴት እንዳለፈ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ጠቅላይ ጸሃፊ አቡነ ሉቃስ ገልፀውልናል።

በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያንም የሕማማት ሰሞን በሃይማኖታዊ ሥነስርዓቶች ይታሰባል። ፓስተር ጻዲቁ አብዶ የኢትዮጵያውያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ናቸው።

የክርስቶስን ግብረ ሕማማት ለምዕመኖቿ ስታስተምር የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ ለትንሳኤ እሑድ አጥቢያ «ለጸሎት ተሰብሰቡ» ስትል የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚሰበሰቡት ምዕመናንም በካህናቱ መሪነት ጸሎት ያደርሳሉ። ምንባቡና ጸሎቱ ካበቃ በኃላም ትንሣኤውን የሚያበሥር ትምህርት ይሰጣል፣ ይዘመራል። ይህ ስርዓት ለእምነቱ ተከታዮች ምን ትርጉም እንዳለው ብፁዕ አባ ኤርሚያስን ጠይቀናቸዋል።

ትንሳዔ የአንድ ቀን በዓል አይደለም የሚሉት የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉቃስም "ትንሳዔ ዳግም ፀጋ ያገኘንበት እንደመሆኑ፣ ፀጋውን መልሰን እንዳናጣው በትንሳኤ የምንኖርበትም ነው" ይላሉ።

በወንጌላውያን ቤተክርስቲያናትም ምዕመናን የትንሣኤውን ብርሃን እንዲያዩ በእለት ተዕለት ኑሮዋቸው የብርሃኑ ተካፋይ እንዲኾኑ እንደሚያስተምሩ ፓስተር ጻዲቁ ያስረዳሉ።

ከፋሲካ በዓል ዋዜማ ጀምሮ የክርስትና እምነት ተከታዮች ወደ ቤተክርስትያን በመሄድ በመጸለይ ፣ በመስገድ፣ እና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በመስማት ያከብራሉ። በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉበት ጊዜ ነውና በሁሉም ቤተክርስቲያናት ለሰላምና ለእርቅ ምህላ እንደሚደረግ የሃይማኖት አባቶች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ የታሰሩ፣ የተፈናቀሉ፣ ሜዳ የወደቁ እና በረሃብ የሚሰቃዩ ሰዎች አሉ የሚሉት ብፁዕ አባ ኤርሚያስ ህዝበ ክርስቲያኑ ይህንን በዓል የተቸገሩትን ሰዎች በመርዳት እና በማገዝ እንዲያሳልፉ ጠይቀዋል።

"ጥላቻ እና መለያየት የመጨረሻው እድላችን አይደለም። ትልቁ ተስፋችን ትንሳዔ ነው" የሚሉት የአቡነ ሉቃስ ምክርም ተመሳሳይ ነው።

ፓስተር ጻዲቁም ተመሳሳይ መልዕክት ያስተላልፋሉ።

ሌሊቱን በየቤተክርስቲያናቱ በጸሎት ያሳለፉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱ ከተበሰረ በኃላ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ። በጾም እና በጸሎት ያሳለፉም እንደየአካባቢው ልማድ እና ባህል ከዘመድ አዝማድ ጋር ተሰባስበው ይፈስካሉ። እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ እየተባባሉም በዓሉን በደስታ ያሳልፋሉ።

XS
SM
MD
LG