በመንግሥት እና በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት “አከራካሪ” እየተባሉ በሚጠሩ አካባቢዎች ከጦርነቱ በኋላ የተቋቋሙት አስተዳደሮች፣ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚፈርሱ ከፌደራልም ኾነ ከክልሉ መንግሥት የተገለጸላቸው ነገር እንደሌለ፣ የወልቃይት ጠገዴ፣ የራያ አላማጣ እና የጸለምት አካባቢዎች አስተዳደሮች አስታወቁ፡፡
ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡት የአካባቢዎቹ አመራሮች፣ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርእሰ መስተዳደር ሌተናንት ጀኔራል ታደሰ ወረደ የተሰጠው መግለጫ፣ “የአንድ ወገን ፍላጎት የተንጸባረቀበት ፕሮፓጋንዳ እና ለሌላ ደም አፋሳሽ ግጭት መቀስቀስ ምክንያት የሚኾን” ሲሉ ተችተዋል፡፡
ለማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች፣ በሕግ እና በመርሕ ላይ የተመሠረተ መፍትሔ እንዲሰጥም አመራሮቹ በአጽንዖት ጠይቀዋል፡፡