በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጎንጂ ቆለላ ወረዳ መምህራን ላለፉት ሁለት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ገለጹ


የጎንጂ ቆለላ ወረዳ መምህራን ላለፉት ሁለት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ገለጹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:33 0:00

በሰሜን ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ፣ ላለፉት ሁለት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው የገለጹ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚኾኑ መምህራን፣ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናገሩ፡፡

በወረዳው በሚገኙ 52 የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩት መምህራኑ፣ ኑሯቸውን የሚገፉት በወርኀዊ ደመወዛቸው ብቻ በመኾኑ፣ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ልጆቻቸው የሚላክ ገንዘብን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ እንደተሳናቸው ገልጸዋል፡፡ በተለይ፣ ለመጪው ዓመት በዓል አስቤዛዎችን ለመግዛት እንደማይችሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ችግሩ መኖሩን ያመኑት የቆንጂ ቆለላ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ደገፋው፣ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሒሳብ ሠራተኞች ቢሮ ገብተው ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመኾናቸው የተፈጠረ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት፣ ከመምህራን ማኅበር ጋራ በመነጋገር ዐዲስ ሠራተኞች ተመድበው ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ጎንጅ ቆለላ ወረዳ፣ በደኅንነት ስጋት ስማቸው በይፋ እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጎንጂ ቆለላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር፣ ካለፈው ወር ጀምሮ የደመወዝ ክፍያ በመቋረጡ ችግር ላይ መውደቃቸውን ነግረውናል፡፡

በዚያው ወረዳ የገረገራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የኾኑትና ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ መምህር፣ ባለፉት ሁለት ወራት ደመወዝ ባለመከፈሉ መጪውን በዓለ ፋሲካ ያለጾም መፍቻ እንደሚያልፉት ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት፣ በክልሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያው እንቅስቃሴ ላይ ችግር መፍጠሩን፣ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን/ኢሰመኮ/፣ ባለፈው ጥቅምት መጨረሻ ባወጣው ሪፖርቱ፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ የተለያዩ ወረዳዎችን የሚያገናኙ የየብስ መጓጓዣዎች በመቋረጣቸው፣ በቁጥርም ውስን በመኾናቸው የተነሣ፣ በንግድ እና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን ማመልከቱ ይታወሳል።

ችግሩ መኖሩን ያመኑት በሰሜን ጎጃም ዞን የጎንጂ ቆለላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ደገፋው፣ በጸጥታ ችግር ምክንያት የሒሳብ ባለሞያዎች ቢሮ ገብቶ ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመኾናቸው መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

ከወቅቱ የጸጥታ ችግር አኳያ ስማቸውን በይፋ እንዳንጠቀስ የጠየቁን የጎንጂ ቆለላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እና የወረዳው የመምህራን ማኅበር አባል መኾናቸውን የገለጹልን አስተያየት ሰጪ፣ በወረዳው ከአንድ ሺሕ በላይ መምህራን በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በምኅጻሩ ዩኤን-ኦቻ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው፣ በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት፣ በምሥራቅ እና በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ዞኖች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ 89 በመቶ የሚኾኑቱ ተዘግተው ይገኛሉ።

በአማራ ክልል በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ከሚገባቸው ተማሪዎች 35 በመቶ የሚኾኑት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውንም፣ የኦቻ ሪፖርት ጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG