በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአውሮፓ ኅብረት የቪዛ አሰጣጥ ለውጥ ላይ በብራስልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምላሽ ሰጠ


በአውሮፓ ኅብረት የቪዛ አሰጣጥ ለውጥ ላይ በብራስልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምላሽ ሰጠ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:28 0:00

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ ለኢትዮጵያውያን የሚደረገውን የቪዛ አሰጣጥ ሒደት ለማጥበቅ እንደወሰነ ማስታወቁን ተከትሎ፣ ትላንት ማክሰኞ ማምሻውን በቤልጂየም-ብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥቷል።

ኤምባሲው፣ ትላንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ የኅብረቱን ውሳኔ “አስደንጋጭ” በማለት ጠርቶታል።

ኅብረቱን ከውሳኔው ላይ ያደረሰው፣ ኢትዮጵያ፣ በሕገ ወጥ መንገድ በአውሮፓ ኅብረት ሀገራት የሚቆዩትን ዜጎቿን በማስመለስ ረገድ የምታደርገው ትብብር፣ “በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ” መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

የድጋሚ ጥያቄን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ምላሽ አለማግኘቱን የጠቀሰው የኮሚሽኑ መግለጫ፣ የአውሮፓ ኅብረት “ከሀገር መባረር” ሲል የሚጠራውን በፈቃደኝነትም ኾነ በበጎ ፈቃደኝነት ያልተመለሱ የመመለሻ ሥራዎችን በማደራጀት ተልዕኮዎች ጉድለቶች መኖራቸውን አስረድቷል፡፡

በአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚቆዩ አብዛኛዎቹ ሰዎች፣ ምንም ዓይነት ሕግ ሳይተላለፉ በአየር መንገዶች እና በወደቦች ወደ አውሮፓ እንደሚገቡ ኮሚሽኑ ገልጾ፣ የቆይታ ጊዜያቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ወደ ቤታቸው አይመለሱም፤ ብሏል፡፡ የእነዚኽ አኀዝም፣ በባሕር በጀልባዎች አማካይነት ተጉዘው በመምጣት ጥገኝነት ከሚጠይቁት አሊያም የተሻለ ኑሮ እና ሥራ ፍለጋ ወደ አውሮፓ ከሚጓዙት እንደሚበልጥ አስታውቋል።

በውሳኔው መሠረት፣ ኢትዮጵያውያን በ27 የአውሮፓ ሀገራት ለመጓዝ በሚያቀርቧቸው የጉብኝት መስፈርቶች መሟላቶች ላይ፣ ከአሁን በኋላ በነጻ የመንቀሳቀስ የነጻነት ፈቃድ አይሰጣቸውም፡፡ በተጨማሪም፣ ከአንድ ጊዜ በላይ ለመመላለስ የሚችሉበትን ቪዛ አያገኙም፡፡ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችም ለቪዛ አገልግሎት እንዲከፍሉ የሚያዝዝ ሲኾን፣ ቪዛ ለማግኘት 15 ቀናትን ብቻ ይወስድ የነበረውን ጊዜ ወደ 45 ቀናት የሚያሳድግ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤትን ርምጃ “አስደንጋጭ” ሲል የገለጸው በብራስልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ኅብረቱ ውሳኔውን እንዲያጤን በመግለጫው ጠይቋል።

የምክር ቤቱ ውሳኔ፣ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስና መልሶ ለማቀላቀል እየተደረገ ያለውን ጥረት ያላገናዘበ ነው፤ ሲል ወቅሷል፡፡ ኤምባሲው አያይዞም፣ “የዜጎችን ማንነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን አታካች ሒደት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ ነው፤” ብሏል።

ጥብቅ እንደኾኑ የተገለጹት የአሁኑ የምክር ቤቱ ማሻሻያዎች፣ ሕገ ወጥ ስደትን ለመግታትና መደበኛ ዝውውሮችን ለማበረታታት የአውሮፓ ኅብረት የሚከተለው አካሔድ አካል ናቸው።

ኅብረቱ በዚህ ወር፣ የጥገኝነት አሰጣጥ እና የፍልሰት ደንቦቹን ማሻሻያ አጽድቋል። ይህም፣ ከጎርጎርሳውያኑ 2026 ጀምሮ በሥራ ላይ ሲውል፣ የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከርና ለጥገኝነት ብቁ ያልኾኑ ኢመደበኛ ስደተኞችን ለመመለስ ያለመ ነው።

ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ኅብረት፣ በጋምቢያ ላይ፣ ተመሳሳይ ጥብቅ የቪዛ ሒደት መመሪያዎችን በሥራ ላይ አውሏል።

የኅብረቱ የቪዛ ሕጎች በሀገራት ላይ የሚተገበሩበት መንገድ፣ እነዚያ ሀገራት ስደተኞችን ለመመለስ በሚያደርጉት ትብብር ላይ የተመሠረተ መኾኑን ምክር ቤቱ አጽንዖት ሰጥቶበታል።

ባለፈው መስከረም፣ ኢትዮጵያ፣ እ.አ.አ. በ2020 እና በ2021 ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከታቀዱት ዜጎቿ መልሳ የተቀበለችው 10 በመቶዎቹን ብቻ እንደነበር ተመልክቷል።

የአሜሪካ ድምፅ፣ በአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ፣ ወደ ኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስልክ ቢደውልም፣ መሥሪያ ቤቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይኾን ቀርቷል።

XS
SM
MD
LG