በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓመቱ የ30 ከመቶ የመንገደኞች ጭማሬ እንደሚጠብቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ


የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርባስ A350-941 አውሮፕላን ዙሪክ አየር መንገድ ላይ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርባስ A350-941 አውሮፕላን ዙሪክ አየር መንገድ ላይ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር አንሥቶ እስከ መጪው ሰኔ ወር ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ በ30 ከመቶ ብልጫ ያለውን የመንገደኞች ቁጥር ለማጓጓዝ ማቀዱን፣ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው፣ ዛሬ ረቡዕ ከሮይተርስ ጋራ ባደረጉት ቆይታ፣ አየር መንገዱ 30 ከመቶ ተጨማሪ መንገደኞችን የሚያገኘው፣ ዐዲስ መሥመሮችን በመጀመሩና ዓለም አቀፍ ጉዞ ዳግም በማንሰራራቱ መሆኑን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ፣ በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከአውሮፕላኖች አቅርቦት መዘግየትና ከአቅርቦት ሰንሰለት መቃወስ ጋራ ተያይዞ በተፈጠረ የሞተር እጥረት ምክንያት ችግሮች እንደተጋረጡበት፣ አቶ መስፍን ጨምረው ገልጸዋል።

“ብዙ ፈተናዎች አሉብን፤” ያሉት አቶ መስፍን፣ “ለምሳሌ፥ የአውሮፕላን አምራቾች በተለይ ቦይንግ፣ አቅርቦታቸው በመዘግየቱ ከፍተኛ የአውሮፕላን እጥረት አለብን፤” ሲሉ አስረድተዋል።

ከፍተኛ የአቅርቦት ችግር የሚስተዋለው፣ በተለይ ከቦይንግ በሚመጡ ጠባብ አካል ባላቸው የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ እንደሆነ አቶ መስፍን ጠቅሰዋል፡፡ ግዙፍ አውሮፕላኖች ለረጅም ርቀት በረራዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መከልከላቸውም ለጉዳት እያጋለጠን ነው፤ ብለዋል፡፡

እ.አ.አ. ሰኔ 2023 በተጠናቀቀው ዓመት፣ 13ነጥብ9 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናገደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በዚህ ዓመት በበረራ ላይ እያለ የበር መገንጠል አደጋ የደረሰበትን የቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች እንደማይጠቀምባቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ የቦይንግ ኩባንያ፣ የደኅንነት ስጋቶቹን ለመፍታት እንደሚችልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። “እነዚህን ሁሉ ለማስተካከል ቦይንግ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ብለን እናምናለን፤" ብለዋል አቶ መስፍን።

በቦይንግ የአቅርቦት ችግር ምክንያት ግን፣ አየር መንገዱ 146 አውሮፕላኖችን፣ ኤይርባሶችንና የካናዳ ሥሪት የሆኑትን ደ-ኻቪላንድ አውሮፕላኖችን፣ ከሚጠበቅባቸው 150 ደረጃ በታች እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝ አቶ መስፍን አክለው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እ.አ.አ በ2035 ያሉትን አውሮፕላኖች እና የበረራ መሥመሩን በዕጥፍ ለማሳደግ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት፣ 70 የቦይንግ እና ኤርባስ አውሮፕላኖችን ያዘዘ ሲሆን፣ ተጨማሪ 54 አውሮፕላኖችን የመግዛት አማራጮችም አሉት። የእድገት ዕቅዱን ዓመታዊ ገቢንም በ400 ከመቶ እና የመንገደኞችን ቁጥር በ440 ከመቶ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ፣ አየር መንገዱ በተያዘው የበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስተናገዳቸው መንገደኞች ቁጥር፣ የዘንድሮውን የእድገት ግብ ለመምታት በሚያስችለው መንገድ ላይ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ይህም፣ ዓመታዊ ገቢን በ20 በመቶ ከፍ በማድረግ ወደ 7ነጥብ3 ቢሊዮን ማድረስንም ይጨምራል።

“ወደተለያዩ መዳረሻዎቻችን የምናደርገውን የበረራ መጠን በመጨመር የበረራ አድማሳችንን እያሰፋን ነው፤” ያሉት አቶ መስፍን፣ ወደ ለንደን ጋትዊክ፣ ማድሪድ እና ባንጊ የተዘረጉ ዐዲስ መዳረሻዎችን በምሳሌነት አንሥተዋል።

አቶ መስፍን አክለው፣ አየር መንገዱ በጭነት ማጓጓዝ ሥራው ላይም ተጨማሪ መዋዕለ ነዋይ እያፈሰሰ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው የካቲት ወር፣ በዋና መቀመጫው አዲስ አበባ፣ በ55 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለኢንተርኔት ላይ ግብይት እና የሸቀጦች ማጓጓዣ የሚሆን ተቋም መክፈቱን ተናግረዋል።

“በኢንተርኔት ላይ የሚደረግ ንግድ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው፤” ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ፍላጎቱ በአፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደመጣ አመልክተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG