በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ሠራተኞች በችግሮች እየተፈተኑ መኾኑን ኢሠማኮ ገለጸ


የኢትዮጵያ ሠራተኞች በችግሮች እየተፈተኑ መኾኑን ኢሠማኮ ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:38 0:00

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከጦርነት፣ ግጭት እና ኑሮ ውድነት ጋራ በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ፈተና ላይ መውደቃቸውን፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፈደሬሽን(ኢሠማኮ) አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፈደሬሽን(ኢሠማኮ)፣ ከነገ በስቲያ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበረውን “የዓለም ሠራተኞች ቀን” አስመልክቶ፣ ዛሬ ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ በቀጠለው የእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት፣ ሠራተኞች፥ ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለእገታ አደጋዎች እየተዳረጉ መኾናቸውን አመልክቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኮንፈደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ሠራተኛው በኑሮ ውድነትም ከፍተኛ ችግር እየደረሰበት እንደኾነ ገልጸው፣ ይህን ችግር ያቃልላሉ የተባሉ ጥያቄዎች ግን ከመንግሥት ምላሽ አላገኙም፤ ብለዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል፣ በሰዎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን፣ የኢኮኖሚ ተቋማት መውደማቸውን፣ ሠራተኞችም ከእነቤተሰቦቻቸው መበተናቸውንና እስከ አኹንም ለማገገም የሚያስችል ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በቀጠሉት ግጭቶች ምክንያትም፣ የልማት ተቋማት ተረጋግተው መሥራት እንዳልቻሉ የተቆሙት ኃላፊው፣ ግጭትቹ ቆሞው ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ፕሬዚዳንቱ አቶ ካሳሁን ፎሎ ጠይቀዋል።

በየጊዜው በልዩ ልዩ ምክንያቶች እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት፣ የሠራተኛውን ሕይወት እንዳከበዱበት የተናገሩት አቶ ካሳሁን፣ የሠራተኛው የሥራ ግብር እንዲቀነስና ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን፣ ለመንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል። በችግሮቹ አፈታት ላይ፣ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶር.) ጋራ ውይይት ቢያደርጉም መፍትሔ እንዳልመጣ ጠቁመዋል።

ከሁለት ቀናት በኋላ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚከበረው የዓለም ሠራተኞች ቀንም፣ ሰላም እንዲመጣ በመወትወት፣ የኑሮ ውድነቱ እንዲሻሻል በመጠየቅ እንደሚከበር፣ የኮንፈዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል፡፡

በዓሉ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሞ ባህል ማዕከል አዳራሽ እንደሚከበር የተናገሩት አቶ ካሳሁን፣ የአደባባዮች አከባበር እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡ “ይህንም ያደረግነው በመንግሥት ተከልክለን ሳይኾን በራሳችን ውሳኔ ነው፤” ሲሉም አክለው አስረድተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG