ዛሬ ሰኞ ንጋት ላይ፣ በአዲስ አበባ ኀይለኛ ዝናም መዝነሙን ተከትሎ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11፣ ወረገኑ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ የጎርፍ አደጋ፣ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የከተማዋ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
ጽ/ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባሰፈረው መግለጫ፣ የከተማ አስተዳደሩ ማስተር ፕላናቸውን ያልተከተሉ የወንዝ ዳርቻ ግንባታዎች፣ ኅብረተሰቡን ለጎርፍ አደጋ እንደሚያጋልጡ በጥናት በመለየት ችግሩን ለመፍታት እየሠራ ይገኛል፤ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ጠባይ ክትትል ባለሞያ አቶ በቃሉ ታመነ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ በአዲስ አበባ እንዲህ ዓይነት ችግር ያጋጠመው፣ ወቅቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናም የሚጥልበት በመኾኑ ነው፤ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ይኸው በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ ሰዎችን ለችግር እየዳረገ ያለውን ጎርፍ የሚያስከትል ዝናም ወደፊትም ሊቀጥል ስለሚችል፣ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ባለሙያው አቶ በቃሉ ታመነ መክረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤትም፣ በከተማዋ መሰል አደጋዎች እንዳያጋጥሙ፣ ኅብረተሰቡ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከእሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልእክቶችን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡
በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም፣ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ወራት የሚዘንመውን የበልግ ዝናም ተከትሎ የጎርፍ አደጋ ሊከሠት እንደሚችል፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ በምኅጻሩ ዩኤን-ኦቻ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የበልጉን ዝናም ተከትሎ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ አካባቢዎች መለየታቸውን ቢሮው አስታውቆ፣ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችም ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወኑ ናቸው፤ ብሏል፡፡