በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሱዳን ኤምሬትስን በጠብ አጫሪነት ከሰሰች


ፎቶ ኤኤፍፒ (ሚያዚያ 3፣ 2024)
ፎቶ ኤኤፍፒ (ሚያዚያ 3፣ 2024)

ሱዳን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን በጠብ አጫሪነት በመክሰስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቃለች፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ምንጮችን ጥቅሶ የኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደዘገበው ከሆነ፣ ሱዳን ኤምሬትስን፣ ከሠራዊቷ ጋራ በመፋለም ላይ ያሉትን የፈጠኖ ደራሽ ኃይሎች በመደገፍ ከሳለች፡፡

ሱዳን ለወራቶች ኤምሬትስን የፈጠኖ ደራሽ ኃይሎችን በመደገፍ ስትከስ ቆይታለች፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ክሱን ታስተባብላለች፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚገኙት የሱዳን ቋሚ መልዕክተኛ ጥያቄውን ለፀጥታው ም/ቤት በሣምንቱ መጨረሻ ማስገባታቸውንና ይህም “ኤምሬትስ ለፈጠኖ ደራሽ ኃይሎች መሣሪያዎችን በማቀበል የጠብ አጫሪነት ተግባር ፈጽማለች” የሚል እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል።

ሱና የተሰኘው የሃገሪቱ ዜና ወኪልም የሱዳን ቋሚ መልዕክተኛ አል ሃሪት ኢድሪስ ለፀጥታው ም/ቤት ጥያቄውን ማስገባታቸውን አረጋግጧል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ለፀጥታው ም/ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ የሱዳንን ክስ አስተባብሏል።

የፀጥታው ም/ቤት በበኩሉ በሰሜን ሱዳን ዳርፉር ክልል እየተባባሰ የመጣው ውጊያ እንዳሳሰበው በትላንትናው ዕለት ገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG