በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን ስለ ጽንስ ማስወረድ ለመነጋገር ፍሎሪዳ ናቸው፣ የትረምፕ የኒው ዮርክ ፍርድ ሂደት ዐዲስ ምዕራፍ ይይዛል


ባይደን ስለ ጽንስ ማስወረድ ለመነጋገር ፍሎሪዳ ናቸው፣ የትረምፕ የኒው ዮርክ ፍርድ ሂደት ዐዲስ ምዕራፍ ይይዛል
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:49 0:00

ባይደን ስለ ጽንስ ማስወረድ ለመነጋገር ፍሎሪዳ ናቸው፣ የትረምፕ የኒው ዮርክ ፍርድ ሂደት ዐዲስ ምዕራፍ ይይዛል። የቪኦኤ ዘጋቢ ቬሮኒካ ባልደራስ ኢግሌሲያስ ያጠናቀረችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

ዛሬ ሰኞ በመክፈቻ ንግግሮች የተጀመረው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የፍርድ ሂደት ዐዲስ ምዕራፍ ይይዛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ስለ ሥነ ተዋልዶ መብቶች ለመናገር ነገ ማክሰኞ በታምፓ ፍሎሪዳ የምርጫ ዘመቻ ያደርጋሉ።

ከሕዝብ የተመረጡ ዳኞች ፣ አቃብያነ ሕጎች እና የዶናልድ ትረምፕ የመከላከያ ቡድን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በማንሃተን፣ ኒው ዮርክ በተከሰሱበት የአፍ ማስያዥያ ገንዘብ ወንጀል ዛሬ ሰኞ የመክፈቻ መግለጫዎቻቸውን ይሰጣሉ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2016ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት ከጋብቻ ውጭ ግንኙነት ነበረን የሚሉ ሴቶችን አፍ ለማስያዝ የሰጡትን የገንዘብ ክፍያ ለመደበቅ በተደረገው ሙከራ ሚና ነበራቸው በሚል 34 የወንጀል ክሶች ቀርበውባቸዋል። ለዘንድሮው አጠቃላይ ምርጫ የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ እጩ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ትረምፕ ክሶቹን ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ትራምፕ ውንጀላውን ሲያጣጥሉ፣ "ይህ በታሪክ እጅግ የከፋውን ፕሬዚዳንት እያሸነፈ ያለውን የምርጫ ዘመቻ ለመጉዳት በመሞከር የሚደረግ ትልቅ መሰረት ቢስ ውንጀላ ነው። ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአገራችን ታሪክ እጅግ የከፋው ፕሬዚዳንት ናቸው። በጣም በብዙ እየረታኋቸው ነው። ሊያሸነፉ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ይህ ብቻ መሆኑን ያስባሉ፡፡ ነገር ግን አይሠራም፡፡" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት የነበረው መጥፎ የአየር ጠባይ ትረምፕ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በኖርዝ ካሮላይና ሊያደርጉት የነበረውን የምርጫ ዘመቻ እንዲሰረዙ አስገድዷቸዋል፡፡

ከዚህ በተለየውና በተከሰሱበት ሌላ የፌደራል ምርጫ ጣልቃ ገብነት ጉዳይ፣ የፕሬዚዳንት ያለመከሰስ መብት ሊሰጣቸው ለምን እንደሚገባ የተከራከሩበትን ሙግትም ባላፈው ቅዳሜ ትሩዝ ወደ ተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረካቸው ወስደውታል፡፡

በዚያ ጉዳይ ላይ የሚደረገው የቃል ክርክር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 25 በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይደመጣል። አንዳንድ ዲሞክራት መራጮች ጉዳዩን በቅርበት እየተመለከቱ ሲሆን፣ የበለጠ ሊነሳሱ ይችላሉ ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ታድ ቤልት ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ሲኾኑ፣ ጉዳዩን የሚከታተሉትን መራጮች በሚመለከት ሲናገሩ "ይህ ከዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ጋራ ያለው ግንኙነት አነስተኛ ነው፣ ምክንያቱም ብዙዎቹ የፈላጭ ቆራጭነት ዝንባሌ አላቸው፣ ብዙዎቹም እንደ ፕሬዚዳንት ያሻቸውን ሁሉ ማድረግ እንዲችሉ ይፈልጋሉ። ባይደን የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲያደርግ፣ ለዲሞክራሲ ስጋት የሆነን ሰው ወደ ስልጣን መመለስ አትችሉም - የሚለውን ግልጽ አድርገዋል፡፡”ብለዋል።

በድጋሚ ለመመረጥ የሚወዳደሩት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተቃናቃኛቸውን የሕግ ተግዳሮቶች ከመጥቀስ መቆጠቡን ቀጥለውበታል።

ባላፈው ዓርብ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የፖለቲካ መልዕክታቸውን አቅጣጫ ወደ ዓለም አቀፍ የኢሌክትሪክ ሠራተኞች ወንድማማችነት አድርገዋል፡፡

ባይደን በንግግራቸው ፣ "ከኔ በፊት የነበሩት፣ ለአሜሪካውያን ሠራተኞች የነበረውን ጥበቃ ቀልብሰዋል። የፌደራሉን ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ ተቃውመዋል። በሚገርም ሁኔታ እሳቸው ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ ባለጸጎችን የጠቀመ፣ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶችን የፈጠረ፣ የፌደራሉ እዳ ከመጠን በላይ ባፈነዳው የ2 ትሪሊዮን ዳላር ግብር ቅነሳ ይኮራሉ፣ በጣም ይኮራሉ፡፡

በጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ የመንግስት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሃንስ ኖኤል በሠራተኛ ማኅበራት የታቀፉ ሠራተኞች ሁለቱም ፕሬዚዳንታዊ እጩዎች ሊያሸንፏቸው የሚገባቸው ከወደየትኛውም ወገን ሊያጋድሉ ከሚችሉ የመራጮች ቡድን መካከል አንዱ እየሆኑ መጥተዋል ይላሉ፣ “ታውቃላችሁ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ፣ ከዚህ ቀደም የናንተን ዓላማ ሲደግፍ የቆየ ፓርቲ ነው የሚለው ፣ በዚህ ቀን እንደገና ሊያስታውሱት የሚገባ ነገር ሆኗል ፤ ባይደን ድምጻቸውን የሚፈልጉት ከሆነ፡፡ ትረምፕም በመጠኑ ትንሽ ለየት ያለ ስለ ስደተኝነት፣ ስለ ባህል የመሳሰሉትን መልዕክት ይዘው እነዚያው ተመሳሳይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋራ እየሄዱ ነው"

ትረምፕ በዚህ ሳምንት የወንጀል ችሎቱ ላይ በአካል መገኘት አለባቸው። በምርጫ ዘመቻው ድረ-ገጽ ላይ እንደተገለጸው እኤአ እስከ ግንቦት 11 በዋይልድ ውድ፣ ኒው ጀርሲ ውስጥ እስከሚደረግ ድረስ ምንም የምርጫ ዘመቻ ዝግጅት አይኖርም፡፡

የባይደን የምርጫ ዘመቻ ለቪኦኤ እንደተናገረው ፕሬዚዳንቱ ማክሰኞ በታምፓ ፣ ፍሎሪዳ - እኤአ በ2024 ምርጫ ከፍተኛ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ - በመላ ሀገሪቱ ስላለው የሥነ ተዋልዶ ነፃነት ንግግር ያሰማሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG