በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን መመለስ ተጀመረ


በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን መመለስ ተጀመረ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:37 0:00

በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች እና ማቆያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን፣ በዘመቻ ወደ አገር ቤት የመመለስ ሥራ፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሯል፡፡ በዛሬው ዕለት በተደረጉ ሁለት በረራዎችም፣ 842 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸው ተገልጿል። ከተመላሾቹ መካከል የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች፣ ከጉዞ ጀምሮ እስከ እስር ቤት ፈታኝ ጊዜያትን ማሳለፋቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት ከሰንበቴ አካባቢ ለሕገ ወጥ ጉዞው መነሣቱን የሚያስታውሰው ናስር መሐመድ፣ በጅቡቲ በኩል የአደን ባሕረ ሰላጤን በጀልባ አቋርጦ ረዥሙንና አስቸጋሪውን የበረሓ መንገድ ተጉዞ የሳዑዲ አረቢያ ደንበር ላይ ሲደርስ መያዙን ይገልጻል፡፡ በጉዞው ወቅት “በበርካታ አስከሬኖች ላይ ተረማምደናል፤ በፍልሰተኞችም ላይ ጥይት በተደጋጋሚ ይተኮስ ነበር፤” ይላል ናስር፡፡ አያይዞም፣ “እኔና ሰባት ጓደኞቼ ይህን ኹሉ እንደምንም አልፈን ደንበር ላይ ብንደርስም ተይዘን በቀጥታ ወደ እስር ቤት ተወስደናል፤” ብሏል፡፡ የእስር ቤት ቆይታቸውም በቂ ምግብ፣ ውኃ፣ ሕክምና የሌለበት እጅግ አስከፊ እንደነበረና ብዙዎች በእስር ቤቱ ሳሉ ሕይወታቸው እንዳለፈም አስረድቷል፡፡

ከአገር ከመውጣቱ በፊት፣ “ስለ ሕገ ወጥ ፍልሰት አስከፊነት ሰዎች የሚያወሩት እውነት አይመስለኝም ነበር፤ አሁን ግን በራሴ ላይ ደርሶ አይቻለኹ፤” የሚለው ናስር፣ ማንም ሰው ይህን አማራጭ እንዳይከተል መክሯል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም መሰል ሐሳብ አጋርተውናል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ፣ በሳምንት 12 በረራዎችን በማድረግ በአራት ወራት ውስጥ ከ70ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ከተመለሱ በኋላ፣ ከክልሎች ጋራ በመተባበር መልሶ የማቋቋም ሥራ እንደሚሠራም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG