በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሁለት “ጽንፈኛ" ያላቸውን የፋኖ አመራሮች መግደሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ


ሁለት “ጽንፈኛ" ያላቸውን የፋኖ አመራሮች መግደሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:54 0:00

በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ፣ ዛሬ ዐርብ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ፣ መንግሥት “ጽንፈኛ” እያለ የሚጠራው የፋኖ ታጣቂ ቡድን “አመራር እና አባላት ናቸው” ያላቸውን ሁለት ግለሰቦች መግደሉን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ግለሰቦቹን ረዘም ላለ ጊዜ ሲከታተላቸው እንደቆየ ገልጸዋል።

ዛሬ ረፋድ፣ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በነበረው እንቅስቃሴ በተደረገ የተኩስ ልውውጥም፣ አንድ የቡድኑ አመራር እና አንድ አባሉ ሲገደሉ፣ ሌላው ደግሞ ያለጉዳት መያዙን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ሚሊኒየም አዳራሽ አቅራቢያ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ፣ መንግሥት “ጽንፈኛ” እያለ የሚጠራው የፋኖ ታጣቂ ቡድን “አመራር እና አባላት ናቸው” ባላቸው ግለሰቦች ላይ ርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡

መግለጫውን በተመለከተ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ባገኘው መረጃ መሠረት ግለሰቦቹን ሲከታላቸው መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

በጸጥታ ኀይሎች እይታ ውስጥ ነበሩ ያሏቸውን እነዚኽን ግለሰቦች፣ በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ሥር ለማዋል በነበረው ሒደትም የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በዚኽም፣ የ“ጽንፈኛው ፋኖ” ያሏቸው አንድ አመራር እና አንድ የቡድኑ አባል መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦቹን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3፣ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ ለመያዝ በተደረገው እንቅስቃሴ፣ የ“ጽንፈኛ”ው ፋኖ መሪ ነበር የተባለው ናሁሠናይ አንዳርጌ ታረቀኝ እና የቡድኑ አባል ነበር የተባለው ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ፣ በተኩስ ልውውጥ መሀል መገደላቸውን፣ ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል፡፡ አቤኔዘር ጋሻው አባት የተባለ የቡድኑ አባል ደግሞ ሳይቆስል በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ሦስቱም ግለሰቦች፣ የሱዙኪ ዲዛየር ተሽከርካሪን በመጠቀም በፖሊስ ላይ ተኩስ መክፈታቸውንና ለማምለጥም መሞከራቸውን መግለጫ አመልክቷል፡፡

ግለሰቦቹ፣ በአዲስ አበባ ከተማ “የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ተልእኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ ነበር” ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው፡፡

“የጽንፈኛ ፋኖ ቡድን አባላት ናቸው፤” ከተባሉት ግለሰቦች በተጨማሪ፣ እንዳሻው ጌትነት የተባሉ ግለሰብ፣ “የጽንፈኛውን ቡድን አባላት አልተባበርም” በማለታቸው በታጣቂዎቹ እንደተገደሉ መግለጫው አስፍሯል፡፡ በተኩስ ልውውጡ፣ በሁለት የፖሊስ አባላት ላይም ጉዳት መድረሱን፣ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

የሟቾቹን ቤተሰቦችና የፋኖ አመራሮችን ለማግኘት ያደርግነው ጥረት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ አልተሳካልንም። እንደተሳካልን ይዘን እንመለሳለን

XS
SM
MD
LG